11ኛው ሀገር አቀፍ የአብሮነት ቀን በሀዋሳ ከተማ ተከበረ

101

ሐዋሳ ጥር 16/2013 (ኢዜአ) 11ኛው ሀገር አቀፍ የአብሮነት ቀን በሲዳማ ክልል ሐዋሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ተከበረ።

 የአብሮነት ባህላችን ለዘላቂ ሰላማችን በሚል ሀሳብ ዛሬ በሀዋሳ የተከበረው የአብሮነት ቀን በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በሲዳማ ብሔራዊ  ክልላዊ መንግስት  ትብብር  የተዘጋጀ  ነው።

በመድረኩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሁሉም ክልሎች ተወካዮች፣ አባገዳዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና ሴቶች  አደረጃጀቶችና የህዝብ ተወካዮች ታድመዋል።

በበዓሉ መክፈቻ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ቡዝነሽ መሠረት እንዳሉት የአብሮነት ቀን የመከበሩ ዋንኛ ምክንያት የዓለም ህዝቦች በመልከዐ ምድር አቀማመጥ፣ በቀለም፣ በኃይማኖት፣ በጎሳና በቋንቋ ልዩነቶች ምክንያት  በየጊዜው በሚፈጠሩ  ግጭቶችና አለመግባባቶች የሚያስከትሉትን መጠነ ሰፊ ጉዳት አጉልቶ በማሳየት ለማስገንዘብ ነው።

በተለይ አንዱ የሌላውን ሰብዓዊ መብት በማክበርና ከሌሎች ጋር በመቻቻል መኖር ለህዝቦች እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ግንዛቤ ለማስረፅ ጭምር እንደሆነ ገልፀዋል።

"በሀገራችን የመቻቻል ቀን ስናከብር በአብሮነት መኖር መርሆዎችን በማስተማር ቅድመ አያቶቻችን ያቆዩልንን ተከባብሮና ተፈቃቅዶ የመኖር ባህላችንን ግንዛቤ በማስጨበጥ  ነው" ብለዋል።

"በተለይ አንዱ የሌላውን ማንነት የማክበር ባህል ሳይሸራረፍ እንዲቀጥል የማድረጉ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ መሆኑን በማሳወቅ ልዩነቶችን በመግባባትና በሠላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ ለማስቻል መድረኩ መማማሪያ ይሆናል" ያሉት።

የሲዳማ ክልል ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘው በበኩላቸው የሲዳማ ህዝብ በሰው ልጅ ማህበራዊ ህይወት ውስጥ አይቀሬ የሆነውን ግጭት የሚፈታበት አፊኒ” የተሰኘ ብርቅዬ የእርቅ ሥርዓት ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።

አፊኒ እስከ ነፍስ ግድያ ያሉ ጥፋቶች እውነታውን በጥሞና በመመርመር እርቅ ማውረድና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አባገዳ ቃበቶ ኤደሞ እና አቶ ተፈራ ሌዳሞ በሰጡት አስተያየት መቻቻል ከሌለ ሰላምም ሆነ ልማት ስለማይኖር ሁሉም አንድነቱን እንዲያጠናክር የአብሮነት ቀን መከበሩ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም