በአዲስ አበባ በ285 ህንፃዎች ላይ በቅርቡ በተደረገ ቁጥጥር በርካቶቹ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጋቸውን ለንግድ እያዋሉት ነው

95

ጥር 16/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በ285 ህንፃዎች ላይ በቅርቡ በተደረገ ቁጥጥርና ፍተሻ አብዛኛዎቹ ለመኪና ማቆሚያ የተሰራውን ፓርኮቻቸውን ወደ ተለያዩ የንግድ ቤቶች ቀይረዋል፡፡

በከተማዋ የሚገነቡ ህንፃዎች የመኪና ማቆሚያ /ፓርኪንግ/ እንዲያካትቱ ህግ የሚያስገድድ ቢሆንም በርካቶች ተግባራዊ እያደረጉት አይደለም ተብሏል።

የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ጂሬኛ ሂርጳ፤  ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማዋ የህንፃ ግንባታ ሲካሄድ ፓርኪንግ መስራትም ግደታ ነው።

በኮንስትራክሽን ላይ የሚገኙ በርካታ ህንጻዎች በዲዛይናቸው የመኪና ማቆሚያ እንዲያካትቱ ቢደረግም ስፍራውን ለንገድ ሱቅ የሚያውሉት በርካቶች ናቸው ብለዋል።

በዚህም ሳቢያ በከተማዋ እየተስተዋለ ላለው የትራፊክ መጨናነቅ ተጨማሪ ችግር እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡

ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ከ285 በላይ ህንጻዎች ላይ ቁጥጥር ተደርጎ በርካታ ህንጻዎች ከህጉ ውጭ እየሰሩ መሆኑን አረጋግጧል።

በርካታ ህንፃዎች ለመኪና ማቆሚያ ያስገነቡትን ስፍራ ለተለያዩ አገልግሎቶች አውለውት ተገኝተዋል።

በመሆኑም ችግሩን ለማቃለል በኤጀንሲው በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ኢንጂነር ጂሬኛ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም 53 የሚሆኑ ሕንጻዎች ማስተካከያ በማድረግ ለመኪና ማቆሚያነት የገነቡትን ስፍራ ለፓርኪንግ እንዲያውሉ ተደርጓል።

ሌሎች 40 የሚሆኑት ደግሞ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተፅፎባቸዋል ነው ያሉት።

ማስተካከያ በማድረግ ትእዛዙን ለመፈጸም በሂደት ላይ የሚገኙ ያሉ ሲሆን ወደ ስራ ላልገቡት ደግሞ በንግድ ቢሮ በኩል ንግድ ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ አረጋግጠዋል።

ከዚህ ባለፈ ህጉን በማያከብሩ የህንጻ ባለቤቶች ላይ ከንግድ ቢሮ፤ ከግንባታና ቁጥጥር ተቋምና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቀጣይ የተጠናከረ ቁጥጥርና እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

የከተማዋን የመኪና ማቆሚያ ግንባታ አገልግሎት ዘመናዊ ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ እና በፌደራል መንግስት ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመዲናዋ ማስተር ፕላኑን ተከትሎ በወሎ ሰፈር፣ ሾላ እና ቸርችል ጎዳና አካባቢ ዘመናዊ ፓርኪንጎች እየተገነቡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የትራፊክ መጨናነቁን ለማቃለል ኤጀንሲው የተገደበ የፓርኪንግ አገልግሎት በአስራ አምስት ቦታዎች ላይ ተግባራዊ ማድረጉንም ጠቅሰዋል፡፡

በአዲሱ ገበያ ዊንጌት ከፒሳ አያት መንገድ ወደ ካራ ወሰን 15 መንገዶች ላይ ክልከላው ተግባራዊ መደረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም