ከአማራ ክልል ወደውጭ ከተላኩ ምርቶች 234 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኘ

59
ባህር ዳር ሀምሌ 17/2010 በተጠናቀቀው በጀት አመት ከአማራ ክልል ወደውጭ ከተላኩ የግብርናና ኢንዱስትሪ ምርቶች 234 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የክልሉ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አፈወርቅ ለኢዜአ እንደገለጹት ገቢው የተገኘው ለገበያ ከተላከው ከ2  ሚሊዮን ኩንታል በላይ የቅባት፣ የጥራጥሬ፣ የአበባና ሌሎች የኢንዲስትሪ ምርቶች ሽያጭ ነው። በተጨማሪም  ከ23 ሺህ 792 የዳልጋ ከብቶችና በግና ፍየሎች እንዲሁም ከ2 ሺህ 752 ቶን የአበባ ምርት ሽያጭ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ። የግብርና ምርቶቹ የተላኩት ወደ ጣሊያን፣ ቻይና፣ ኔዘርላንድስ፣ እስራኤል፣ አሜሪካ፣ ቤልጂየም፣ ግሪክ፣ እንግሊዝ፣ ህንድና ሌሎች ሀገራት እንደሆነ ተናግረዋል። እንደ ምክትል ሀላፊው ገለጿየግብርና ምርቶቹ ወደውጭ የተላኩት በዩኒየኖች፣ በባለሃብቶችና  በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት አማካኝነት ነው፡፡ ከተላኩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች የተገኘው ገቢ ከቀዳሚው በጀት ዓመት በ96 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ብልጫ አለው ። በአካባቢው የተረጋጋ ሰላም መፈጠሩ፣ የቁም እንስሳት ለገበያ መላክ መጀመራቸውና በዓለም ገበያ የግብርና ምርቶች ዋጋ መነቃቃት ለገቢው ማደግ አስተዋፆ ማድረጉን አስረድተዋል ። የፀሐይ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ በሰጡት አስተያየት ዩንየኑ በበጀት አመቱ ወደ ውጭ ከላከው 26 ሺህ 400 ኩንታል የሰሊጥ ምርት 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝቷል ። በተያዘው በጀት ዓመት 50 ሺህ ኩንታል የሰሊጥ ምርት ወደውጭ በመላክ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን አመላክተዋል ። ዩኒየኑ በ2009 በጀት ዓመት ወደውጭ ከላከው 8ሺህ 550 ኩንታል የሰሊጥ ምርት 1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማስገኘቱን አስታውሰዋል። በተጠናቀቀው በጀት አመት 1ሺህ 440 ኩንታል ነጭ ቦሎቄ ወደ ቤልጂየም በመላክ 120 ሺህ 240 የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የገለጹት ደግሞ የራስ ጋይንት ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ መልካሙ ፈንታሁን ናቸው።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም