በህብረተሰቡና ባለድርሻዎች ተሳትፎ በተከናወነ የሰላምና ጸጥታ ስራ አበረታች ውጤት ተገኝቷል- አቶ ኦርዲን በድሪ

90

ሐረር ጥር 16/ 2013 (ኢዜአ) በሀረሪ ክልል በህብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በተከናወነ የሰላምና የጸጥታ ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስታወቁ::

በክልሉ በተከናወኑ የጸጥታ ስራዎች አስተዋጽዎ ላበረከቱ ባለድርሻ አካላት ምስጋናና  እውቅና ተሰጥቷል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ማህበረሰብ፣ በጸጥታ አካላት፣ በሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት  አባቶች እንዲሁም  በገለልተኛ  አማካሪና  በሰላም ቤተሰብ በሚሰሩ  የሰላምና የጸጥታ  ስራዎች አመርቂ ውጤት  እየተመዘገበ ነው::

"በተለይ በክልሉ ባለፉት ጊዜያት የተከናወኑ ሃይማኖታዊ በዓላትና ሌሎች ስነ ስርአቶች  ያለጸጥታ ችግር በሰላም መከበራቸው ህብረተሰቡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኝነት በግልጽ  ያሳየ  ነው" ሲሉ ተናግረዋል::

በቀጣይ ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት  ለሰላምና ጸጥታ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን አስቀድሞ ለመከላከል ከጸጥታ አካላት ጋር የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ማጎልበት  ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል።

በመነጋገርና በውይይት ችግሮች እንዲፈቱ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ሊጎለብቱ  እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ቀጣይ የሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ፍታሃዊ፣ ነጻ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ  እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡም ሆነ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንዲያበረክቱ  ርዕሰ መስተዳደሩ ጠይቀዋል::

በክልሉ ይታዩ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች ተቀርፈው የቀድሞው የመቻቻል ፣የሰላምና  የአብሮነት ባህል መመለሱን  የጠቀሱት ደግሞ የክልሉ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ  ሃላፊ አቶ ናስር ዮያ ናቸው።

"ለተገኘው ውጤት የጸጥታ አከላት፣ ብረተሰቡና የፖሊስ አጋዥ ሃይሎች  ላበረከቱት  አስተዋጽዎ ምስጋና ይገባቸዋል" ብለዋል።

ህብረተሰቡ፣ የጸጥታ አካላት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና  ሌሎች  ባለድርሻ አካላት ቀን ከለሌት ተቀናጅተው ያስገኙት ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበለጠ መትጋት እንደሚገባ አስገንዘበዋል ።

የእውቅና ሰርተፍኬት ከተበረከተላቸው ተቋማት መካከል በኢትዮዽያ  ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የምስራቅ ሐረርጌና የሐረሪ ክልል ሀገረ ስብከት አንዱ ነው።

የሀገረ ስብከቱ ዋና ስራ አስኪያጅ  መላከ ገነት ቀሲስ  ንጋቱ ደሳለኝ  እንደተናገሩት  የእውቅና ሰርተፍኬቱ ለተቋማቱ ትልቅ ድጋፍ ይሰጣል::

"የተሰጠው እውቅና ቤተ እምነቶች ማህበረሰቡና ምዕመናኑ  ይበልጥ በመተሳሰብ፣  በመካባበርና  በአንድነት እንዲኖሩ የሚያከናውኑትን የአስተምህሮት ስራ  አጠናክረው  እንዲቀጥሉ መነሳሳትን ይፈጥራል" ብለዋል።

የሐረሪ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ሊቀመንበር ሀጂ ቶፊቅ አብደላ  በበኩላቸው "ለምዕመናን ስለሰላምና አንድነት በመስበካችን በክልሉና በማህበረሰቡ መካከል ሰላም እንዲፈጠር፣ መቻቻልና አብሮነት እንዲጎለብት አድርገናል" ብለዋል።

"የእውቅና ሽለማቱም በቀጣይ ይበልጥ እንድነሰራ አነሳስቶናል፤ እኛም ይህን ለመተግባር ሳንሰለች እንሰራለን "ሲሉም ተናግረዋል።

በሐረሪ ክልል ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና በክልሉ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት በጋራ  በተዘጋጀው ስነ ስርአት ለሃይማኖት ተቋማት፣ ለጸጥታ አካላት፣ ለመገናኛ ብዙሀን ተቋማት፣  ለወረዳ መስተዳድር፣ ለሰላም ቤተሰብና አምባሳደር  ለገለልተኛ አማካሪ  ቡድን  ምስጋናና  የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም