"በኢትዮጵያ አንድ ብሄር ብቻውን የሚኖርበት መሬት አይኖርም" - አቶ ደመቀ መኮንን

83

ጥር 15/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ አንድ ብሄር ብቻውን የሚኖርበት መሬት አይኖርም ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

በመተከል የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት መንግስት የአካባቢውን ነዋሪዎች አሰልጥኖ በማስታጠቅ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በቻግኒ ራንች የተፈናቃዮች መጠለያ ተገኝተው ከተፈናቃዮች ጋር ተወያይተዋል።

ተፈናቃዮቹ ከመኖሪያ ቀያቸውና ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው መጠለያ ከገቡ በኋላ ከመንግስት የሚደረግላቸው ሠብዓዊ ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ይህ ብቻም አይደለም መንግስት የዕለት ሠብዓዊ እርዳታ ከማቅረብ ባለፈ አካባቢውን በፍጥነት ከስጋት ቀጠና አውጥቶ በዘላቂነት ወደቀድሞ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል።

በመሆኑም መንግስት በመተከል እየተፈጸመ ላለው ኢ-ሠብዓዊ ድርጊት ትኩረት በመስጠት በቶሎ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል።

ለመጪው ክረምት ማምረት ካልቻሉ በርካታ ዜጎች ለረሃብ ይዳረጋሉ፤ መንግስትም ድጋፍ ለማድረግ ይቸገራል ያሉት ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት ወደ ቦታችን እንመለስ ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለተፈናቃዮች የሚያስፈልገው ሠብዓዊ ድጋፍ በተቻለ መጠን እንዲቀርብ ይደረጋል፤ ውስንነቶች ካሉም ይስተካከላል ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሰሜን ክፍል፣ በአንዳንድ የጎረቤት አገራት ወደ ጦርነት የመገፋትና ሌሎች ችግሮች በየትኛውም አቅጣጫ ቢከሰት ከመተከል የሚበልጥ ባለመሆኑ የመንግስት ሙሉ ትኩረት መተከል ላይ ነው ብለዋል።

በመተከል የንጹሃን ዜጎች ጭፍጨፋና የንብረት ውድመት የሁሉንም ቅስም የሰበረ አሳዛኝ ክስተት በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ጥብቅ ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ በየትኛውም አካባቢ ሌሎች ብሄሮችን አጽድቶ አንድ ብሄር ብቻውን የሚኖርበት መሬት አይኖርም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን።

መተከል በአሁኑ ወቅት በጠቅላይ ሚኒስትሩ በተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል እንጂ በፖለቲካ አመራሩ እንደማይተዳደር አስታውሰው፤ ከዚህ በኋላ የዜጎች እሮሮና ጩኸት ይቆማል ብለዋል።

በመተከል ግጭቱን በመምራትም ሆነ በማስተባበር እንዲሁም በቸልተኝነት የንጹሃን ህይወት እንዲጠፋ ንብረታቸው እንዲወድም ያደረጉ አመራሮች እየተለዩ ለሕግ ይቀርባሉም ነው ያሉት።

ኅብረተሰቡም እነዚህን የግጭት ነጋዴ የስራ ሃላፊዎችና ግለሰቦች ለመንግስት አጋልጦ በመስጠት መተባበር እንዳለበት አሳስበዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን መንግስት የመተከልን የሠላም እጦት በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉንም የአካባቢውን ሕዝብ ያማከለ ሚሊሻ በማሰልጠን ራሱን እንዲጠብቅ ያደርጋል ብለዋል።

መንግስት አሰልጥኖ የሚያስታጥቃቸው ሚሊሻዎች በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና ይሁንታን ያገኙ ብቻ ይሆናሉም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም