ተመራቂዎች የሀገሪቱን የብልጽግና ጉዞ ለማሳካት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ

1691

ሀዋሳ ፤ጥር 15/2013 (ኢዜአ ) ፡- ተመራቂ ተማሪዎች ሀገሪቱን ለመለወጥ መንግስት እያካሄደ ያለውን የብልጽግና ጉዞ በትምህርት ባገኙት ዕውቀት በማገዝ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተመለከተ። 

ወራቤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 1ሺህ 77 ተማሪዎችን ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ በወቅቱ  ባደረጉት ንግግር በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ውስጥ የበኩር ተመራቂ በመሆናችሁ ልዩ ናችሁ ብለዋል።

ተመራቂዎች ሀገሪቱን ለመለወጥ መንግስት እያካሄደ ያለውን የብልጽግና ጉዞ ለማገዝ በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት ተግባር ላይ በማዋል የደርሻቸውን እንዲወጡ አመልክተዋል።

የበለጸጉ ሀገራት የተሻለ ህብረተሰብዊ ለውጥ ማምጣት የቻሉት በርካታ የተማረ የሰው ሀይል ይዘው ለመምራት ስለቀለላቸው መሆኑን  ተናግረዋል።

ሀገራችንም ለትምህርት ስራ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን  በማስፋፋት ዕውቀትና ክህሎት ያለው ሀይል ለማፍራት እየሰራች የምትገኘው ለዚህ ነው ብለዋል።

ተማሪዎች በሰለጠኑበት የትምህርት መስክ ሀገራቸውን በቅንነት ለማገልገል በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አቶ ሀይለማሪያም አሳስበዋል።


የወራቤ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ቶፊቅ ጀማል በበኩላቸው በ2010 ዓ.ም¸ የማስተማር ሥራ ጀምረው  አምና የመጀመሪያ ተማሪዎቹን ለማስመረቅ ዝግጅት እያደረጉ ባለበት ወቅት የኮሮና ክስተት እንዳስተጓጎለው አስታውሰዋል።

ዘንድሮ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው ፕሮቶኮል መሰረት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብለው በአጭር ጊዜአ ውስጥ የማካካሻ ትምህርት በመስጠት ለምረቃ እንዳበቁ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ባሉት አራት ኮሌጆች በ14 የትምህርት መስኮች ከተቀበላቸው ተማሪዎች ውስጥ ዛሬ 1ሺህ 77 ተማሪዎችን ማስመረቃቸውንና ከመካከላቸውም 465 ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል አራት ነጥብ በማምጣት በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው እመቤት ቱፋ በሰጠችው አስተያየት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በማለፍ ለዚህ በመብቃቷ ደስተኛ እንደሆነች ተናግራለች።

በተማረችበት የሙያ መስክም ሀገሯን በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነችም ገልጻለች።

ሌላው የማዕረግ ተመራቂ ፍትህአወቅ በፍርዱ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመቋቋም ለዛሬ ቀን በመብቃቱ መደሰቱንና ባቀደው መሰረት ጥሩ ውጤት ይዞ ለመውጣት እንደቻለ ተናግሯል።

ወራቤ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በ49 የትምህርት መስኮች ከአራት ሸህ የሚበልጡ ተማሪዎችን እያስተማረ እንደሚገኝ ተመልክቷል።