መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ሺህ 324 ተማሪዎችን አስመረቀ

124

ጎባ ፤ ጥር 15/2013 (ኢዜአ)፡-- መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ኮሮናን በመከላከል በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ያሠለጠናቸውን ሁለት ሺህ 324 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ። 

በምረቃው ሥነ-ሥርዓቱ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አህመድ ከሊል እንደተናገሩት ተማሪዎች የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አልፈው በዩኒቨርሲቲው የተሰጠውን የገጽ ለገጽ የማካካሻ ትምህርት ወስደው ለምረቃ በቅተዋል፡፡

በተለይ ኮሮናና ሀገራዊ የፀጥታ ችግሮች መሰናክል ቢፈጥሩም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ጭምር በመጠቀም ትምህርታቸውን ተከታትለው እንዲመረቁ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ተማሪዎች በመደበኛ፣ ማታና ክረምት መረሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆኑን ገልጸው ከመካከላቸውም  902 ሴቶች እንደሆኑ አመላክተዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራችውንና ህዝባቸውን ማገልገል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ተመራቂዎች በተለያዩ ውጣ ውረድ ውስጥ በማለፍ የቀሰሙትን እውቀትና ክህሎት ለሀገር ግንባታ በማዋል የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

ሀገሪቱ  ብዙ ውጣ ውረድ አልፋ ለምረቃ የበቁት  ብዙዎች በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት በሥራ ቦታቸው የሚያጋጥማቸውን ተግዳሮት በብቃት በመወጣት ሀገርን እንዲያሻግሩ ዶክተር ሳሙኤል አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ስራ ፈጠራ ኮሚሽነርና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከአንድነታችን ይልቅ ልዩነታችን ጎልቶ የሚታያቸው ቡድኖች ዩኒቨርሲቲዎቻችንን የላቀ ሀሳብ ማመንጫና የእውቀት መቅሰሚያ እንዲሆኑ ከማድረግ ይልቅ የልዩነት ግንብ መገንቢያ አውድማ እንዲሆኑ ሲሰሩ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

በተለይ ማንነትን መሰረት ያደረጉ የግጭት ችግር  መፍትሄ በሚመነጭባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢም አሳፋሪም ያደርጓል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አቶ ንጉሱ የዘንድሮ ተመራቂዎች በሚሰማሩበት የሥራ ዘርፍ የኢትዮጵያን አንድነትና ሠላም እሴቶችን ከሚፈታተኑ ጽንፈኝነትና ዘረኝነት ጸድተው ሀገራቸውን በተማሩት ሙያ በታማኝነት እንዲያገለግሉ መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል።

በዩኒቨርሲቲው አራት ነጥብ በማምጣት የሜዳሊያና ዋንጫ ተሸላሚ  በመሆን የተመረቀው ቱራ አራርሳ በሰጠው አሰተያየት  ኮሮና  በትምህርታችን ላይ ጫና ቢያሳድርም ተቋቁመን መመረቅ በመቻላችን ተደስተናል ብሏል፡፡

በተማረበት የሙያ ዘርፍ ህብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልገል፣ የኢትዮጵያን አንድነትና ሠላም ለማስጠበቅም የድርሻውን እንደሚወጣም ገልጿል፡፡

ሁሉም በየተሰማራበት ጠንክሮ ከሰራ ያቀደውን ውጤት ማምጣቱ አይቀርም ያለችው ደግሞ በዩኒቨርሲቲው ከሴቶች መካከል ከፍተኛ ነጥብ አምጥታ የዋንጫና ሌሎች የማበረታቻ ሽልማቶች ያገኘችው ፋንቱ ነጋሽ ናት፡፡

 የተለያዩ ውጣ ውረዶች በያጋጥማትም አስተማሪዎችና ቤተሰቦቸው ባደረጉላት እገዛ ለስኬት በመብቃቷ መደሰቷንም ገልጻለች፡፡

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት በየደረጃው የሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል፡፡

በ1999 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሥራውን  የጀመረው መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮን ጨምሮ ከ30ሺህ በላይ  ተማሪዎችን  ማስመረቁን በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም