ህገ መንግስቱ ለሴቶች ያጎናጸፋቸውን መብቶች ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል - አቶ አደም ፋራህ

76

አዳማ፣ ጥር 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) ህገ መንግስቱ ለሴቶች ያጎናጸፋቸው እኩል የመጠቀም መብታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚኖርበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ -ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

"የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ለፌዴራል ሥርዓቱ መጎልበት ያለው ሚና" በሚል ርዕስ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለ ድርሻ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሄዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዳሉት፤ የህገ መንግስቱ የበላይነት እንዲረጋገጥና መንግስታዊ ሥርዓቱ እንዲዳብር በእኩልነትና መፈቃቀር ላይ የተመሰረተ አገራዊ አንድነት እንዲጠናከር እየተሰራ ነው።

ሴቶችን በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ እኩል እንዲሳተፉና ተጠቃሚነታቸው ለማረጋገጥም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

"በህገ መንግስቱ የተደነገገውን የእኩልነት መብት ለማጎልበት የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ትልቅ ጠቀሜታ አለው" ሲሉ አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።

ከለውጡ ወዲህ ሴቶች በመልካም ሁኔታ ወደ አመራርነት መምጣታቸውን አውስተዋል።

አሁንም አነስተኛ የሆነውን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሻሻል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሁሉም በላይ ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

ህገመንግስቱ ለሴቶች ያጎናጸፋቸው የእኩልነት መብት እንዲረጋገጥና ከፌዴራል ሥርዓቱ በፍትሃዊነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚኖርበትም ገልጸዋል።

ሴቶችም የፖለቲካ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ተደራጅተው ለመብታቸው መታገልና የሚያገኙትን ዕድል በአግባቡ በመጠቀም በአገሪቱ የዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲጎለብት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

መንግስትም የሴቶችን መብት ለማስከበር የሚሰሩ የሲቪክና የብዙሀን ማህበራትን መደገፍ፣ ተሳትፏቸውን የሚያጠናክሩ የህግና ፖሊሲ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚኖርበትም አቶ አደም አመልክተዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ ፖለቲከኞች በበኩላቸው ሴቶችን በፖለቲካ በማሳተፍና በማብቃት ረገድ ያለውን ሰፊ ክፍተት ለማስተካከል እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ አቅም ማጎልበት ላይ መሰራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም