ምክር ቤቱ በሕግ ማስከበር ዘመቻ ጉዳት ለደረሰባቸው የሠራዊቱ አባላት ድጋፍ አደረገ

1511

ጥር 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ተግባር ምክር ቤት በትግራይ ክልል በተካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ጉዳት ለደረሰባቸው የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሚውል የ160 ሺህ ዶላር እና 2 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።

የምክር ቤቱ ጸሐፊና የልዑካን ቡድኑ መሪ አቶ ዳዊት ጋላሶ በተለያዩ አገሮች የሚኖረው ዳያስፖራ የአገሩን ሁኔታ በንቃት እየተከታተለ መሆኑን ገልጸዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት ኢትዮጵያን ለመበታተን በህወሓት ጁንታ በኩል የሚነዙ ፕሮፓጋንዳዎች በዳያስፖራው ዘንድ ስጋት ፈጥረው እንደነበረ አስታውሰዋል።

ይሁንና በአገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስት በወሰደው ሕግ የማስከበር እርምጃ ስኬታማ ሥራ መከናወኑ ኢትዮጵያዊያኑን ከስጋት እንዲወጡ ማድረጉን አንስተዋል።

ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ስድስት ወራት ያስቆጠረ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳዊት፤ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ከ364 ሺህ ዶላር በላይ ማሰባሰቡን ገልፀዋል።

ከዚህ ውስጥ 160 ሺህ ዶላር ዛሬ በመከላከያ ሚኒስቴር ተገኝተው ያስረከቡ ሲሆን ቀሪውን በአጭር ጊዜ እንደሚያስረክቡ ነው የተናገሩት።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው የምክር ቤቱ አባላት በአጭር ጊዜ ድጋፍ አሰባስበው አጋርነታቸውን በማሳየታቸው አድንቀዋል።

ዳያስፖራው ባለው ዕውቀትና ገንዘብ ለኢትዮጵያ ልማትና ገጽታ ግንባታ የተሻለ ሥራ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የዘሉሲ ትሬዲንግ አክሲዮን ማኅበር ለመከላከያ ሠራዊት 85 ሺህ ብር አበርክቷል።

የማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ረታ ነግሬው “በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃት አገር ከማጥፋት የማይተናነስ ነው” ብለዋል።

የማኅበሩ አባላት ከዕለት ጉርሳቸው ቀንሰው ከሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት ያደረጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።

ወይዘሮ ማርታ የሕግ ማስከበር ዘመቻው ውጤታማ የሆነው በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ርብርብ መሆኑን ገልፀው፤ በየቦታው የተበታተኑ የጁንታውን አባላት መልቀምና ክልሉን መልሶ የማቋቋም ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።