ተመራቂዎች የጋራ እሴቶችን በማጎልበት የሃገራቸውን የቀደመ ታላቅነት ለመመለስ እንዲጥሩ ጥሪ ቀረበ

69

ጎንደር፣ ጥር 15/2013(ኢዜአ ) ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው የጋራ እሴቶችን በማጎልበት የሃገራቸውን የቀደመ ታላቅነት ለመመለስ ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ። 

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ  ተማሪዎችን ዛሬ ባስመረቀበት ወቅት የተገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር እንዳሉት ሃገር የምትገነባውና ወደ ታላቅነት ማማ ልትወጣ የምትችለው በሠለጠነ ብቁ የሰው ሃይል ነው።

ትውልዱን በትምህርት በመገንባት  ከተሳሳተ የሴራ ትርክት በመውጣት እንደ ሃገር ጠንካራ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ አቅም መገንባት ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው ብለዋል።

ለዚህም ሀገሪቱ  ከድህነት በማላቀቅ ወደ ብልፅግና ለማራመድ መንግስት ለትምህርት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ልዩነትን በማክበርና የጋራ እሴቶችን በማጎልበት የሃገራቸውን  የቀደመ ታላቅነት ለመመለስ ያልተቆጠበ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በራስ የመተማመን አቅምን በማጎልበት በየደረጃው የሚገጥሙ ችግሮችን በጥበብና እውቀት ተጋፍጦ ለሃገራቸው ታሪክ ሰሪ እንደሆኑም  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ትውልዱ ለሃገሩ ተቆርቋሪና ለብልፅግና የሚተጋ ታማኝ ሆኖ እንዲወጣም የከፍተኛ ትምህርት ተቋምት የድርሻቸውን እንዲወጡም እንዲሁ።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን   በበኩላቸው የዘንድሮ  ተመራቂዎች በቆይታቸው የገጠሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ችግሮችን በማለፍ ለስኬት የበቁ በመሆናቸው ከሌለው ጊዜ የተለያ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል።

እንዳ  ዶክተር አስራት ገለጻ ተቋሙ ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ  በጥናትና ምርምር እንዲሁም  ማህበረሰብ አገልግሎት ድጋፍ በማድረግ ህዝብ የጣለበትን ሃላፊነት እየተወጣ ነው።

ይህን አስቸጋሪ ወቅት በጥበብ፣ ብልሃትና ትጋት መወጣት እንዲቻል  ላገዙ የዩኒቨርስቲው ማህበረሰብ አባላት ምስጋና አቅረበዋል።

ተመራቂዎች ባገኙት እውቀትና ክህሎት ከኢትዮጰያዊነት ዝቅ ሳይሉ ህዝባቸውን በእኩልነትና ፍትሃዊነት እንዲያገለግሉም ዶክተር አስራት አሳስበዋል።

በሲቪል ኢንጅነሪንግ የተመረቀው እራሳቸው ሹሜ በሰጠው አስተያየት ባገኘው እውቀትና ክህሎት የስራ እድል በመፍጠር ሃገሩንና ህዝቡን ለማገልገል መዘጋጀቱን ተናግሯል።

በኮሮና ምክንያት በወቅቱ  የመማር ማስተማር ስራው የተስተጓጎለ ቢሆንም ተስፋ ባለመቁረጥ ትምህርቱን ለማጠናቀቅ በመብቃቱም መደሰቱን ተናግሯል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ትምህርቷን በማጠናቀቅ ለዛሬ  የምረቃ ቀን በመብቃቷ  መደሰቷን የተናገረችው ደግሞ በፐብሊክ ሄልዝ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀችው ደብረወርቅ ተስገራይ ናት።

በሠለጠነችበት የጤና ዘርፍ በምርምር የታገዘ በማድረግ ህብረተሰቡን በቅንነትና ታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ያስመረቃቸው በቁጥር ሰባት ሺህ 293 ተማሪዎች ሲሆኑ የሠለጠኑትም  በህክምና ጤና ሳይንስ፣ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ ህግ፣ ግብርናና ሌሎችም የትምህርት መስኮች ነው፤ ከተመራቂዎቹም መካከል ሁለት ሺህ 489 ሴቶች እንደሆኑ ተመልክቷል።

በምረቃ ሥነ -ሥርዓት የፌዴራል፣ ክልል፣ ጎንደር ከተማ አስተዳደር አመራሮች ፣ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላትና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም