ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ከ4 ሺህ 100 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

145

ደብረማርቆስ፣ ጥር 15/2013 (ኢዜአ) ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ለ12ኛ ጊዜ በመደበኛውና ተከታታይ ትምህርት መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ከ4 ሺህ 100 በላይ ተማሪዎችን በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ዛሬ አስመረቀ።

የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት፤ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተማሪዎች ለረጅም ጊዜ ከትምህርት ገበታ እርቀው ነበር።

ወደ ትምህርታቸው ከተመለሱ በኋላ በተደረገ ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለምርቃት በቅተዋል።

ዩኒቨርሲቲው በደብረማርቆስና ቡሬ ካምፓሶቹ አሠልጥኖ ካስመረቃቸው ተማሪዎች መካከል ከ1 ሺህ 500 የሚበልጡ ሴቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

"200 ተማሪዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች በሁለተኛ ዲግሪ የተመረቁ ናቸው" ብለዋል።

ተማሪዎቹ ተቋርጦ የቆየውን ትምህርት ለማካከስ ተግተው ያገኙትን እውቀት ለአገራቸው ሠላም፣ ዕድገትና ብልጽግና በማዋል የድርሻቸውን መወጣት አንዳለባቸውም አሳስበዋል።

የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የኢፌዴሪ ፕላን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ በበኩላቸው "የአገርን ዕድገት ለማፋጠን ቴክኖሎጂን የታጠቀ የሰው ኃይል ማፍራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል" ብለዋል።

ያደጉ ሀገራት ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመፍጠር የዕድገት ማማ ላይ መድረስ የቻሉት የሰው ሀይል አቅማቸውን በትምህርትና ስልጠና በመደገፋቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዘመኑ የሚያስፈልገውን ቴክኖሎጂን የመፍጠርና የመጠቀም አቅሟን ለማሳደግ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ሀይል ግንባታ ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን አመልክተዋል።

ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው አገራቸው ከድህነት በማላቀቅ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ተመራቂዎች በርካታ ውጣ ውረድን አልፈው ለምረቃ መብቃታቸውን ገልጸዋል።

በተማሩት ትምህርት ስራ ፈጣሪ በመሆን ራሳቸውንና አገራቸውን ለመጥቀም እንደሚጥሩ ተናግረዋል።

የደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የዛሬ ተመራቂዎችን ጨምሮ ባለፉት 12 ዓመታት ከ37 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቁንና በአሁኑ ወቅትም ከ28 ሺህ 900 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምርቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም