መንግስት በዘላቂነት የመተከል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ቁርጠኛ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

1763

ጥር 15/2013 ( ኢዜአ) “መንግስት በዘላቂነት የመተከል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ቁርጠኛ ነው” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከመተከል ከተፈናቀሉ ተጎጂዎች ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።

በውይይቱም ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈናቅለው በቻግኒ ከተማ ራንች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የተጠለሉ አርሶ አደሮች የእለት ጉርስ እየጠበቁ መቆየት እንደሌለባቸው ገልጸዋል።

መንግስት በተቻለ መጠን በፍጥነት ሊያቋቁማቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል።

ለተፈናቃዮቹ ምላሽ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግስት ለዜጎች ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በተለይም በተለያየ ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች ቅድሚያ በመስጠት የማቋቋም ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በውይይቱ ላይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ተስፋዬ ቤልጅጌ፣ የኮማንድ ፖስቱ ዋና አስተባባሪ ሌ/ጄኔራል አስራት ዴኔሮ፣ አርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነን ጨምሮ የፌዴራል እና የክልል የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።