ኅብረተሰቡን ስለ ሠላም ለማስገንዘብ የሃይማኖት ተቋማት የማይተካ ሚና አላቸው ... ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ

84

አዲስ አበባ፣ ጥር 15/2013 (ኢዜአ) ኅብረተሰቡ ስለ ሠላም ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ የሃይማኖት ተቋማት የማይተካ ሚና እንዳላቸው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ምክትል ከንቲባዋ እና የአዲስ አበባ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በመዲናዋ ሠላምና ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከሃይማኖት አባቶችና ከሠላም ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያይተዋል።

ምክትል ከንቲባ አዳነች 'አሁን ያለን ሠላም ከእጃችን ከወጣ ለመመለስ እንቸገራለን' ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ሠላም አጥብቆ በመያዝና ኅብረተሰቡም ስለ ሠላም ያለው ግንዛቤ እንዲጨምር የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛውን ድርሻ መያዝ አለባቸው ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች ኅብረተሰቡን በመግራት ችግሮችን በስሜት ሳይሆን በውይይት መፍታት እንደሚቻል በማስተማር ረገድ የማይተካ ሚና እንዳላቸውም ጠቁመዋል።

የመልካም አስተዳደር እጦትና ብልሹ አሰራሮች ለሠላም እጦት ምክንያት መሆናቸውንም አመላክተዋል።

በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ሠላምን በማረጋገጥ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ለዚህ ደግሞ ከተማ አስተዳደሩ ከሃይማኖት ተቋማትና ከሠላም ምክር ቤት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ነው ያረጋገጡት።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በመንግስት ተቋማት ውስጥ ተቀምጠው ሕዝብን ከሕዝብ፣ ሃይማኖትን ከሃይማኖት ለማጋጨት የሚሞክሩ አካላትን ፈትሾ ማጥራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ወጣቱን በመገፋፋት ወደ አላስፈላጊ ድርጊት እያስገቡ እንደሚገኙ ጠቁመው እነኚህም በሕግ ሊጠየቁ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጁንታው ርዝራዦችና አመለካከቱ ያለቀቃቸው ግለሰቦች በሃይማኖት ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ የመንግስት ሃላፊነቶች ላይ ስላሉ የማጥራቱ ስራ ለነገ የማይባል መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል።

ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ከተማ አስተዳደሩ የሚያስመሰግን ስራ ሰርቷልም ብለዋል።

ሠላም የሁላችን ሀብት ነው ያሉት የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ አለሙ በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ወራት በርካታ የጥፋት ድግሶች ተደግሰው እንደነበረ አስታውሰው በኅብረተሰቡ ሠላም ወዳድነት መክሸፋቸውን ተናግረዋል።

አገራዊ ለውጡ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበ ቢሆንም ችግሮች መኖራቸውን ሃላፊው ተናግረዋል።

የአገር ግንባታን የማጠናከር ጉዳይ የሁሉም ዜጋ የዕለት ተዕለት ተግባር ሊሆን እንደሚገባና የሃይማኖት ተቋማት ድርሻም ከፍተኛ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የተዛቡ አስተሳሰቦችን ለማረቅ ቤተ-ዕምነቶች በመልካም ስነ-ምግባር ቀረፃ ላይ እንዲረባረቡም ጠይቀዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት አመራሩ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው የተበላሹ አመለካከቶችን ከምንጩ ለማድረቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በውይይቱ ማጠናቀቂያ የአዲስ አበባ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔና ከሠላም ምክር ቤት ጋር በፀጥታና ሠላም ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም