በመተከል በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚያደርሱት የጉሙዝ ማኅበረሰብን የማይወክሉ ጽንፈኛ ቡድኖች ናቸው - የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎች

56

ጥር 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመተከል በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚያደርሱት የጉሙዝ ማኅበረሰብን የማይወክሉ ጽንፈኛ ቡድኖች መሆናቸውን የዳንጉር ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

"የጥፋት ቡድኑ ጥቃት እያደረሰ ያለው በማንነት ላይ ብቻ ሳይሆን በአገራዊ ለውጡ ባለው ጥላቻ ነው" ብለዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሰረት ባደረገ ጥቃት ንጹሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፤ ንብረታቸው ወድሟል።

በዚህም በመተከል በተፈጠረው አለመረጋጋት በርካታ ንጹሃን ዜጎች 'ቤት ንብረቴ' ሳይሉ ከኖሩበት ቀዬ ለመፈናቀል ተገደዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተቀናጀ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የአካባቢውን የፀጥታና የሕግ ማስከበር ስራ ከተረከበ በኋላ የችግሩን መንስኤ በመለየት የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል።

ከኅብረተሰቡም ጋር በተለያዩ አካባቢዎች ውይይት እያካሄደ ነው።

ትናንት በዳንጉር ወረዳ ከተለያዩ ቀበሌዎች ከተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ አስተያየት የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ በጫካ መሽጎ ንጹሃንን የሚገድለው ቡድን የጥፋት ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው።

ነዋሪዎቹ "የሽፍታው ቡድን አባላት የእኛው ቤተሰቦች፣ ዘመዶችና የምናውቃቸው ልጆች በመሆናቸው አድራሻቸውን በመጠቆም መተባበር ይገባናል" ሲሉም ተናግረዋል።

በንጹሃን ላይ ጥቃት የሚያደርሱት የጉሙዝን ማኅበረሰብ የማይወክሉ ጽንፈኛ ቡድኖች እንደሆኑም ጠቁመዋል።

የጥፋት ቡድኑ ለውጡን የተቀበለ የጉሙዝ ማኅበረሰብንም ይገድላሉ፤ ጥላቻቸው ከማንነት ጋር ሳይሆን ከለውጡ ጋር ነው ሲሉም ነው የተናገሩት።

ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል በሠራዊቱም ሆነ በክልሉ የፀጥታ ሃይል ስር ያሉ አንዳንድ ሰዎች ሊፈተሹ እንደሚገባም አመልክተዋል።

"ጽንፈኛው ቡድን ብልጽግናን እናጠፋለን ብሎ የተነሳ በመሆኑ በጋራ ልንከላከለው ይገባል፤ ከመከላከያ ሠራዊት ጎንም እንሰለፋለን" ሲሉ ነው የተናገሩት።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሠላም ግንባታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ገለታ ሃይሉ የአካባቢውን ሠላም ለማስጠበቅ ኅብረተሰቡ በጋራ መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በወንጀል የተሳተፉ አመራሮችና ግለሰቦች እየተለዩ ለሕግ እየቀረቡ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሂደቱ የሚቀጥል በመሆኑ ነዋሪዎቹ ወንጀለኞችን አጋልጦ በመስጠት እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

የዳንጉር ወረዳ ኮማንድ ፖስት ሃላፊ ሌተናል ኮሎኔል አስቻለው ይሁኔ በወረዳው ሠላም ለማስፈን ሽፍታውን መደምሰስ ወሳኝነት እንዳለው ገልጸዋል።

የሕግ ማስከበር ዘመቻው በቅርቡ እልባት አግኝቶ ክልሉ ወደነበረበት ሠላምና መረጋጋት እንደሚመለስ ገልጸው፤ ለሽፍታው መረጃ በማቀበል የሚሳተፉ ግለሰቦችን አጋልጦ ለሕግ ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም