የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መሠረታዊ እውቀት ፖሊሲና ስትራቴጂ እየተዘጋጀ ነው

342

አዲስ አበባ፣ ጥር 15/2013 (ኢዜአ) የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መሠረታዊ እውቀት የሚመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ገለጸ። 

የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መሠረታዊ እውቀት /ሚዲያ ሊትሬሲ/ መረጃን እንዴት መፈለግ፣ መሰብሰብ፣ ማጣራት፣ መጠቀምና ማሰራጨት እንደሚቻል የሚያሳይ ነው።

ቴክኖሎጂዎችን እንዴት መጠቀም እንደሚቻልና ከመረጃ ስርጭት ጋር ሊነሱ የሚችሉ የመብትና የሥነ-ምግባር ጉዳዮችንም በቀላሉ ያስገነዝባል።

በኅብረተሰብ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎችና መርሆዎችን በማጎልበት የኋላ ኋላም ሠላምና ደኅንነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደሚያመችም መረጃዎች ያሳያሉ።   

ይህን ከግምት በማስገባት የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መሠረታዊ እውቀት የሚመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን የገለጸው።

የባለሥልጣኑ የጥናትና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ታምራት ደጀኔ እንደተናገሩት፤ በአገሪቷ የሚዲያ አጠቃቀም የሕግ-ማዕቀፍ ባለመኖሩ በዘርፉ በርካታ ችግሮች ታይተዋል።

በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በሚዲያው ዘርፍ በመጣው ነጻነት ሚዲያን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የመጠቀም አዝማሚያዎች በስፋት መኖራቸውን ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎ ባለሥልጣኑ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲና ከመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም /ዩኔስኮ/ ጋር በጉዳዩ ላይ ጥናት ማካሄዱን ጠቁመዋል።

የጥናቱን ውጤት መሰረት በማድረግም የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መሠረታዊ እውቀት የሚመራበት ፖሊሲና ስትራቴጂ እየተዘጋጀ መሆኑን አቶ ታምራት ጠቁመዋል።

ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት የፖሊሲና ስትራቴጂው ይዘት እንዲዳብርና ከሌሎች የዘርፉ የሕግ-ማዕቀፎች ጋር እንዲጣጣም ይደረጋል ብለዋል።  

ፖሊሲና ስትራቴጂው ሂደቱን አልፎ ሲፀድቅ የሚዲያውን ዘርፍ ሙያዊ ሥነ-ምግባር የተላበሰና ኃላፊነት የተሞላበት በማድረግ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆንም ገልጸዋል።

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ምንይችል መሰረት በበኩላቸው የሚዲያ አጠቃቀም መሰረታዊ እውቀት በፖሊሲና ስትራቴጂ ደረጃ የመቀረጹን አስፈላጊነት ገልፀዋል።

በተለይም ሰፊው ኀብረተሰብ የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎችን እንዴት ማግኘት፣ ማመዛዘንና መጠቀም እንደሚችል በማሳወቅ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።  

የሚዲያን መሰረታዊ እውቀት የሚመለከቱ የተበታተኑ ጉዳዮችን በመሰብሰብ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ በአንድ ቋት ለማስቀመጥም ፖሊሲውና ስትራቴጂው እንደሚያግዝ ገልጸዋል።   

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ጌታቸው ጥላሁንም ፖሊሲው የሚዲያ አጠቃቀም ሙያዊና ሃላፊነት ያለበት እንዲሆን ይረዳል ብለዋል።

በተለይም አሁን የሚስተዋለው ሃላፊነት የጎደለው የሚዲያ አጠቃቀም ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም ፖሊሲው መልክ እንደሚያሲዘው ተናግረዋል።

በፖሊሲ ደረጃ መቀረጹም ጉዳዩን ወጥ በሆነ መልኩ በሕግ ማዕቀፍ እንዲመራ ያስችለዋል ነው ያሉት።   

የፖሊሲው መዘጋጀት ለሠብዓዊ ልማት ይጠቅማል ያሉት ደግሞ በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህር እንግዳወርቅ ታደሰ ናቸው።  

ፖሊሲው የሚዲያ አጠቃቀም መሰረታዊ እውቀት ወደ ትምህርት ሥርዓቱ እንዲካተት ስለሚያደርገው ሰዎች ሚዲያን በቅጡ እንዲያውቁ ያስችላል ነው ያሉት።

ይህም በሚዲያ የሚተላለፉ ይዘቶችን፣ የሚዲያ ተቋማትን ፍላጎትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲገመግሙ ያግዛቸዋል ብለዋል።        

በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም መሠረታዊ እውቀት /ሚዲያ ሊትሬሲ/ ፖሊሲና ስትራቴጂ የመጀመሪያው ውይይት ትናንትና በአዳማ ተካሂዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም