የሠላም ሚኒስቴር በመንግስት ግንኙነት እና በአርብቶ-አደር ፖሊሲዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለሚዲያ አካላት እየሰጠ ነው

1518

ጥር 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሠላም ሚኒስቴር በመንግስት ግንኙነት እና በአርብቶ-አደር ፖሊሲዎች ላይ ያተኮረ ሥልጠና ለሚዲያ አካላት እየሰጠ ነው።

ሥልጠናው ዓላማ ያደረገው የሚዲያ አካላት በተለይ ባለሙያዎቹ አገራዊ ሠላም መረጋገጥ የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ “የሠላም ሠራተኞች” በሚል ነው።

ሥልጠናው ከሚኒስቴሩ ተልዕኮ በመነሳት ኢትዮጵያዊ ሠላም ፖሊሲ፣ የመንግስት ግንኙነት ፖሊሲ፣ የአርብቶ-አደር ፖሊሲ እንዲሁም ሠላም ግንባታ የሚሉ የትኩረት ነጥቦችን እንደሚያካትት ተገልጿል።

በሚኒስቴሩ የፌዴራሊዝምና ልዩ ድጋፍ ጀኔራል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ደገፋ ቶሎሳ በመክፈቻው ላይ እንዳነሱት፤ አገራዊ ሠላምን ለማምጣት የፀደቁና ረቂቅ ፖሊሲ ሰነዶች አሉ።

እስከአሁን የአርብቶ-አደር ፖሊሲ ሰነድ ጸድቆ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ አማርኛን ጨምሮ በሌሎች ቋንቋዎች በመታተም ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

የመንግስት ግንኙነት ፖሊሲ መጽደቁን ገልጸው ኢትዮጵያዊ ሠላም ፖሊሲ ደግሞ እየረቀቀ እንደሚገኝ ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።የሰላም ሚኒስትር አማካሪ አቶ ሚናስ ፍሰሐ በበኩላቸው ሠላምን ለማምጣት ወደ ውስጥ መመልከት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

“ለሚዲያ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት የሚኒስቴሩን ተልዕኮ ከማሳካት አልፎ የውስጥ ሠላም ግንባታን ለማምጣት ያስችላል” ብለዋል።

አገር ተኮር፣ ህዝብን ያገናዘበ ተቋምና ኢትዮጵያዊ ሠላምን ለማምጣት ያግዛልም ብለዋል አቶ ሚናስ።

የህግ ማዕቀፍና ተቋማዊ መዋቅር፣ የተጠሪ ተቋማት ጥምረትና የሠላም ፖሊሲና ስትራቴጂ ምንነት ዙሪያ ግንዛቤ እንደሚፈጠር ተጠቁሟል።

ሚኒስቴሩ ተመሳሳይ ሥልጠናዎችንም ለምሁራን፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሐይማኖት ተቋማት እስከ ማህበረሰብ ተኮር ውይይት እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል።