በምሥራቅ ወለጋ ዞን ያረጀ ቡናን የማደስ ሥራ ተጀመረ

82

ነቀምቴ፣ ጥር 15/2013(ኢዜአ) በምሥራቅ ወለጋ ዞን ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በተጓዳኝ ያረጀ ቡናን የማደስ ሥራ መጀመሩን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ሥራው የተጀመረው ትናንት በዞኑ ጉቶ ጊዳ ወረዳ በኤባ ቀበሌ ውስጥ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በዞኑ በቡና ከተሸፈነው ከ185 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ እስከ 30 በመቶው ያረጀ ቡና መሆኑ ተገልጿል።

አርሶ አደሩ ምርቱን በማሳደግ በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራው በተጓዳኝ በ1ሺህ519 ሄክታር መሬት ላይ ያረጁ የቡና ተክሎችን የማደስ ሥራ እንደሚካሄድ የጽህፈት ቤቱ የቡና ልማት ቡድን መሪ አቶ አሰፋ መኮንን ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ውስጥ 120 ሄክታር የሚገኝ ያረጀ የቡና ተክልን በመንቀል በአዲስ ችግኝ የመተካት ቀሪው ደግሞ ባለበት የመጎንደል ሥራ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ስራው በተጀመረበት ጉቶ ጊዳ ወረዳ በ205 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ተክል በተመሳሳይ የማደስ ሥራ እንደሚካሄድ የገለጹት ደግሞ የወረዳው የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መላኩ ጋሪ ናቸው።

በወረዳው የኤባ ቀበሌ አርሶ አደር ተሾመ ገመቹ በሰጡት አስተያየት ያላቸው የቡና ተክል ከአባታቸው የወረሱትና በአሁኑ ወቅት ያረጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአንድ ሄክታር ላይ የቡና ተክል የመጎንደል ስራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደር ታምሩ ዋቅጅራ በበኩላቸው በበሽታና እርጅና ምክንያት ምርት መስጠት ያቆመውን እስከ 800 ያረጁ የቡና ተክሎችን ለማደስ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ያረጁ የቡና ተክልን በመጎንደል ተጠቃሚ እንደሆኑ የተናገሩት ደግሞ ሌላው የቀበሌው አርሶ አደር ቤኩማ የማኖስ ናቸው።

አርሶ አደሩ እንዳሉት በእርጅና ምክንያት ምርት መስጠት ያቆሙትን 100 የቡና ተክሎችን በመጎንደል ወደ አዲስ ለመቀየር ተሰናድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም