የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ከችግር ሊያወጣ የሚችልና አገርን ሊያሻግር የሚችል ሃላፊነት ይጠበቅበታል - አቶ ደመቀ መኮንን

ጥር 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) “የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ከችግር ሊያወጣ የሚችልና አገርን ሊያሻግር የሚችል ሃላፊነት ይጠበቅበታል” ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአራት ኮሌጆች በ22 የትምህርት ዓይነቶች 8 ሺህ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ሲሆን ዛሬ ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎችን አስመርቋል።

437 ሴቶች እና 525 ወንዶች በአጠቃላይ 957 ተማሪዎችን ለምረቃ አብቅቷል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ በአጭር ጊዜ አንጋፋ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የበኩር ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው ‘እንኳን ደስ አላችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል።

‘በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ እኩይ ዓላማ የሚያስፈጽሙ አካላት ከፍተኛ ትምህርትን የግርግር ማዕከል አድርገው እጅግ አሳዛኝ ድርጊት ሲፈጸምባቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው” ብለዋል።

በዚህ ረገድ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ከእንዲህ አይነት ነገር በመራቅ አገርን አክብሮ የምርምርና የእውቀት ማዕድን ለመቅሰም ላሳዩት አረዓያነት በእጅጉ አመስግነዋል።

በቀጣይም ይህንን ባህልና ሃላፊነት መተግበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ከተለያዩ ጥቃቶች፣ መጠፋፋቶች የራቀ አገርን ሊያሻግር የሚችል ምርምር፣ ከችግር ሊያወጣ የሚችል ሃላፊነቶች መውሰድ የሚጠይቅን ስለሆነ ልምዳችሁ ለመጪው ዘመን ተሻጋሪ እንዲሆን ላሳስብ እወዳለሁ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም