የአድዋ ተጓዥ ወጣቶች ደብረ ብርሃን ሲደርሱ አቀባበል ተደረገላቸው

1512

ደብረብርሃን፤ጥር 14/2013(ኢዜአ) የአድዋ ድል በዓልን መታሰቢያ ለማክበር ወደ ሥፍራው በእግር ጉዞ የጀመሩ ወጣቶች ደብረ ብርሃን ከተማ ሲደርሱ በአካባቢው ህዝብና አስተዳደር አቀባበል ተደረገላቸው።

ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተውጣጥተው አዲስ አበባ በመሰባሰብ  ጥር 12/2013 ዓ.ም የእግር ጉዞ የጀመሩ 125 ወጣቶች 130 ኪሎ ሜትር አልፈው ዛሬ ደብረ ብርሃን ከተማ መድረሳቸውን የጉዞው አስተባባሪ ወጣት ደረጀ ገብረዜና ተናግሯል።

አድዋ የህብረ ብሄራዊ አንድነታችን መለያና ከአባቶቻችን የወረስነው የአፍሪካዊያን ዓርማ ነው ያለው ወጣት ደረጀ፤ የአድዋ የድል ቀን መላ አፍሪካዊያን የነፃነት የድል ችቦ የለኮሱበት ነው ብሏል።

ወጣቱ ትውልድ ከአያቶቹና አባቶቹ ጀግንነትን በመማር ኢትዮጵያን ወደተሻለ ብልጽግና ለማሻገር መነሳሳትን ለመፍጠር ዓላማ ያለው ጉዞ እንደሆነም አስረድቷል።

ወጣቶቹ ፍቅርን፣ ሠላምንና አንድነትን በየደረሱበት ለህብረተሰቡ እያስተማሩ እስከ አድዋ ድረስ አንድ ሺህ 110 ኪሎ ሜትር በእግር እንደሚጓዙም ገልጿል።

ወጣቶች ከአድዋ ድል ተምረው ቂምና ቁርሾን በማስወገድ ሀገርን በጋራ ከጠላት ለመከላከልና ለመጠበቅ እንዲነሳሱ የሚኖረው ፋይዳም የጎላ መሆኑን ተናግሯል።

የደብረ ብርሀን ከተማ ነዋሪና የ82 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ወይዘሮ ፈለቃ ገብረአምላክ የአድዋ ተጓዥ ወጣቶች ደብረ ብርሃን ከተማ ሲደርሱ አበባ አበርክተውላቸዋል።

ለወጣቶቹ ባስተላለፉት መልዕክትም የአባቶቻቸውን ታሪክ በማስጠበቅ የሀገራቸውን ዳር ድንበር  እንዲያስጠብቁ መክረዋል።

ከእርስ በእርስ ግጭቶች በመውጣትና አንድነታቸውን በማጠናከር ለሀገራቸው እድገትና ብልፅግና በጋራ እንዲቆሙም  አደራ ብለዋል።

የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ ድባቤ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ለወጣቶቹ አቀባበል ከማድረግ ባለፈ ለጉዞ የሚሆን ውሃና ደረቅ ስንቅ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ተጓዦቹ ከከተማዋ በዘጠኝ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የአጼ ምኒሊክ የተወለዱበትን እንቁላል ኮሶ ተብሎ የሚጠራውን ቦታ እንደጎበኙም ገልጸዋል።

ነገ ደግሞ  አጼሚኒሊክና አፄ ዮሐንስ ስምምነት ያደረጉበትን “ልቼ “የሚባል ታሪካዊ  ቦታን እንደሚጎበኙም ይጠበቃል።

ወደ አድዋ የእግር ጉዞ የጀመሩ ወጣቶችም ከሰመራ፣ ሐረር፣ ባህርዳር፣ አዲስ አበባ፣ ሶዶ፣ ሆሳዕና እና ከሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ መሆናችውም ተመልክቷል።