የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ እንደምታጠናክር ገለጹ

55

ጥር 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የቆየ ወዳጅነት ይበልጥ እንደምታጠናክር ገለጹ።

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ከኬንያ እና ሱዳን ጉብኝታቸው በኋላ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ ይገኛሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ሁለቱን አገሮች ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ ከአቶ ደመቀ ጋር በነበራቸው ቆይታ በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁ ተብራርቶላቸዋል።

በአሁኑ ወቅት ክልሉን መልሶ የመገንባትና የሰብአዊ ድጋፍ ስራዎችም ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸውላቸዋል።

"በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ለሚደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች መንገዶች ሁሉ ክፍት ናቸው" ያሉት አቶ ደመቀ፤ 85 በመቶ በሚሆነው የክልሉ አካባቢዎች የምግብ እና የመድሃኒት አቅርቦት እየተዳረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ የተፈጠረው ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝም አቶ ደመቀ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ስትራቴጂክ አጋር አገሮች እንደመሆናቸው መጠን ችግሩን በሰለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ኢትዮጵያ ፅኑ ፍላጎት ያላት መሆኑንም አረገግጠውላቸዋል።

የህዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር በጋራ መግባባት ላይ ተመስርቶ እንዲካሄድና የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ኢትዮጵያ ጥረት ታደርጋለችም ነው ያሉት።

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ፤ ኢትዮጵያና እንግሊዝ የቆየና እስካሁንም የዘለቀ ጥልቅ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋለ።

እንግሊዝ በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ወዳጅነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሻ አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀጠና ሰላምና መረገጋት እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ ለመደገፍም አገራቸው ፍላጎት እንዳላት ነው የገለጹት።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መንግስት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያና እንግሊዝ ከ70 ዓመታት በላይ የዘለቀ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም