የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

71

አዲስ አበባ ጥር 14/2013 (ኢዜአ) ግሪን አግሮ ሶሊዩሽን የተባለ ተቋም የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሸል የሚረዳ " ሲቢኢ ብር ለእርሻ " የሚል መተግበሪያ ስራ ላይ ለማዋል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ዮሃንስ ሚሊዮን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት "ባንኩ ግብርናውን ማዘመን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ቁልፍ መንገድ መሆኑን በመረዳት በዘርፉ ከተሰማሩ አካላት ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነው"።

መተግበሪያው የአርሶ አደሩን ስራና አኗኗር ከማሳለጡ ባለፈ የቁጠባ ባህሉን እንዲያዳብር እንደሚረዳም ተናግረዋል።

አርሶ አደሩ ባለበት ቦታ አስፈላጊ ግብአቶችን እንዲያገኝ ለማገዝ ከግብርና ግብዓት አምራቶች ጋር ለመስራት ባንኩ ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል።

ቴክኖለጂውን ያበለጸገው የግሪን አግሮ ሶሊሽን የተባለው ተቋም መስራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም እንድሪስ "መተግበሪያው አርሶ አደሩ የገበያ ሁኔታን ጨምሮ ሙያዊ ምክሮችን በሰለጠኑ ባለሙያዎች እንዲያገኝ የሚረዳው መሆኑን" ገልጸዋል።

መተግበሪያው አርሶ አደሩ ያለበትን የመረጃ ክፍተት ከመቅረፍ ጀምሮ የሚገዛቸውን ግብዓቶች በቀላሉ ለማግኘት  እንደሚረዳውም እንዲሁ።

ቴክኖለጂው የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ከማሳለጥ ባለፈ ጥሬ ገንዘብ ይዞ በሚዘዋወርበት ወቅት የሚያጋጥም አደጋን እንደሚቀንስ ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖለጂ ሚኒስቴር ደኤታ ዶክተር አህመዲን አህመድ "ዋነኛው የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ግብርናውን ማዘመን በመሆኑ አርሶ አደሩ በባለሙያ ታግዞ ከሰራ ምርትን በማሳደግ ግሽበትን ማስቀረት ይቻላል ብለዋል።

ተቋማቸውም በቀጣይ ጥናትና ምርምር በማድረግ በዘርፉ ለመስራት ፍላጎት ካላቸው አካላት ጋር አብሮ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መሃመድ ሳኒ ግብርናውን ለማዘመን በዘርፉ የሰለጠኑ ባለሙያዎች እርዳታ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ።

መተግበሪያው ይፋ የተደረገው በአርሲ ዞንና በምዕራብ አርሲ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሲሆን በቀጣይ በሁሉንም አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ቴክኖለጂውን ያበለጸገው ተቋም በግብርና የተመረቁ 81 ወኪሎችን አሰልጥኖ ወደ ስራ ማስገባቱ ተገልጿል።

መተግበሪያው በአማርኛ ፣በኦሮምኛና በእንግሊዝኛ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም