በተሽከርካሪ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ

83

ደብረማርቆስ፣ ጥር 14/2013 (ኢዜአ ) በምስራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ በደረሰ የተሽከርካሪ አደጋ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ። 

የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ክፍል ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ትላንት ለሊት ዘጠኝ ሰአት ላይ ነው።

ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ  ይጓዝ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 -23795 አማ አነስተኛ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ  በወረዳው  “ገሽ”ቀበሌ በመገልበጡ አደጋው መድረሱን ተናግረዋል ።

በአደጋው አሽከርካሪውን ጨምሮ የሁለት ሰዎች ህይወት ወድያው አልፏል።

በሌሎች 13 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።

የአካል ጉዳት የደረሰባቸው በደብረ ማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው።

ህይወታቸውን ያጡት የአሽከርካሪውና የአንድ ተሳፋሪ አስከሬን በሉማሜ የመጀመሪያ ደረጃ  ሆስፒታል መግባቱን  የገለጹት ዋና  ኢንስፔክተሩ አስከሬኑን ወደ የቤተሰቦቻቸው ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

"በሌሊት ህዝብን አሳፍሮ መጓዝ ወንጀል ነው" ያሉት ዋና ኢንሰፔክተሩ በሌሊት ጉዞ ሊደርስ የሚችለው አደጋም የከፋ በመሆኑ አሽከርካሪዎችና ተሳፋሪዎች ከሌሊት ጉዞ ራሳቸውን ማቀብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ መሆኑን ዋና ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም