የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል በወጣው ረቂቅ ላይ የተለያየ አቋም አሳይተዋል

343

አዲስ አበባ፣ጥር 13/2013 (ኢዜአ) የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል በወጣው ረቂቅ መመሪያ ላይ ከ50 ሰዎች በላይ የሚያሳትፉ ስብሰባዎች ሲካሄዱ በጽሁፍ የማሳወቅ ግዴታ መሆኑን በሚገልጸው ነጥብ ላይ የተለያዩ አቋሞችን አራምደዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ በመመሪያው የተካተተው ሃሳብ የጤና ሚኒስቴር ካወጠው መመሪያ የተወሰደ እንጂ ቦርዱ የጣለው አዲስ ግዴታ እንዳልሆነ አብራርቷል።

ቦርዱ በምርጫ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቀነስ እንዲሁም በምርጫ ሂደቶች ላይ  የጸጥታ አስከባሪ አካላት የአሰራር ስርዓትና ስነ-ምግባር አስመልክቶ ባዘጋጃቸው ረቂቅ መመሪያዎች ዙሪያ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከጸጥታ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

በመድረኩም በምርጫ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭን ለመቀነስ የተዘጋጀውን ረቂቅ መመሪያ በሚመለከት ገለጻ ተደርጓል።

በመመሪያው ከ50 ሰዎች በላይ የሚሳተፉባቸው ከምርጫ ጋር  የተያያዙ ስብሰባዎች ፣ ስልጠናዎች እና የምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻዎችን የሚያዘጋጁ አካላት ከሁነቱ ቢያንስ 48 ሰዓታት አስቀድመው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወይም አግባብ ላለው በክልል ወይም በምርጫ ክልል ደረጃ ላለ ጽህፈት ቤት በጽሁፍ የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ያስቀምጣል።

ይህ ሃሳብም በውይይቱ በተሳተፉ አብዛኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታ ቀርቦበታል።

በመመሪያው የተካተተው ሃሳብ በነጻነት የምርጫ ቅስቀሳ እንዳያደርጉ እንቅፋት እንደሚፈጥርባቸው  ነው ፓርቲዎቹ ሃሳብ ያነሱት።

በጽሁፍ የማቅረቡ ሂደትም የተንዛዛ አሰራር እንዲኖር እንደሚያደርግም ጨምረው ገልጸዋል።

በመሆኑም መመሪያው ተግባራዊ መሆን የለበትም ሲሉ ተከራክረዋል።

በመድረኩ በጽሁፍ የሚለው በቃል ማሳወቅ በሚል ተቀይሮ መመሪያው እንዲተገበር ሃሳብ ያነሱ ፓርቲዎችም አሉ።

መመሪያው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ፣ የእጅ ማጽጃ ኬሚካል መጠቀምና አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ መሰብሰብን ግዴታ በሚያደርግ አንቀጽ መሻሻል እንዳለበትም የጠየቁ አሉ።

“የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል የእጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ እንዲቀር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሀሳብ ከምን ላይ ደረሰ?” የሚል ጥያቄም በፓርቲዎቹ ተነስቷል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በበኩላቸው የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ያወጣውን መመሪያ ለማስፈጸም ባወጣው ደንብ ከ50 በላይ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ዝግጅት ሲኖር ለሚኒስቴሩ በጽሁፍ ማሳወቅ ግዴታ መሆኑን አስቀምጧል ነው ያሉት።

በመሆኑም ምርጫ ቦርድ ይህንኑ ደንብ በመከተል በጽሁፍ የማሳወቅ ግዴታን በረቂቅ መመሪያው ማካተቱን ተናግረዋል።

በመመሪያው መሰረት  የኮቪድ-19 ግብረ ኃይል እንደሚቋቋም ጠቁመው፤ ግብረሃይሉም በጽሁፍ ለሚቀርብለት ሃሳብ አፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥበት አሰራር ይዘረጋል ብለዋል።

ቦርዱ የቫይረሱን ስርጭት ለመከለከል የእጩዎች የድጋፍ ፊርማ ማሰባሰብ እንዲቀር የሚጠይቀው ምክረ ሀሳብ  ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ቦርዱ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ የሕግ ማዕቀፎችን ባከበረ መልኩ እንዲካሄድ በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ነው የገለጹት።

ቦርዱ ምርጫ ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቀነስ እንዲሁም በምርጫ ሂደቶች ላይ  የጸጥታ አስከባሪ አካላት የአሰራር ስርዓትና ስነ-ምግባር አስመልክቶ ያዘጋጃቸው ረቂቅ መመሪያዎች በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጸድቀው ተግባራዊ  ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው ስብሰባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ በሚመለከት የቀረበለትን የውሳኔ ሀሳብ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።