”በኦሮሚያ ክልል ሰላም ከማስከበሩ ተግባር ጎን ለጎን የልማት ስራዎች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ማከናወን ተችሏል”

348

አዲስ አበባ፣ጥር 13/2013 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ሰላም ከማስከበር ተግባራት በተጓዳኝ የልማት ስራዎች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የክልሉ የስድስት ወር የስራ አፈጻጸምና ግምገማ በአዳማ ከተማ በገልማ አባገዳ ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የተገኙ ሲሆን በግማሽ ዓመቱ በክልሉ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ  ዘርፎች የተመዘገቡ  ስኬቶችና ተግዳሮቶች ዙሪያ ሪፖርት ቀርቧል።

ያለፉት ስድስት ወራት በአገሪቱም ሆነ ክልሉ የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች እንደነበሩ አቶ ሽመልስ አንስተዋል።

ሆኖም የክልሉ መንግስት ባደረገው ጠንካራ የስራ አመራር ከህግ ማስከበርና ሰላም ማስፈን ጎን ለጎን የልማት ስራዎች በታቀደላቸው ጊዜ መከናወናቸውን ገልጸዋል።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ፣ በክልሉ በማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ በርካታ ተግባራት ከእቅድ በላይ መሳካታቸውን አንስተዋል።

በትምህርት ዘርፍ  የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽነትና ጥራት ከማሻሻል አኳያ በአንድ ክፍል 60 ተማሪዎች ይማሩበት የነበረውን ሁኔታ አንድ ክፍል ለ40 ተማሪዎች መሻሻሉን ገልጸዋል።

በተያዘው አመት የትምህርት ዘርፍ ወንድማማችነት የሚገነባበት እንዲሆን በአጎራባች ክልሎች መካከል ያሉ ትምህርት ቤቶች የተለያዩ ቋንቋዎች እንዲያስተምሩ በማድረግ ስኬት መመዝገቡን አንስተዋል።

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ፣ የኮሮናቫይረስን መከላከል ስራዎች መከናወናቸውንም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንትና የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ እንዳሉትም እቅዶች ከዚህ በፊት እንደነበሩት ብቻ መጨረሻ ላይ የሚገመገሙ ሳይሆን፤ በየወሩ ክትትል ሲደረግባቸው መቆየቱን ገልጸዋል።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ በየዘርፉ የተመዘገቡ ውጤቶች እንዳሉ ሆነው በተለይ በግብርናው ዘርፍ ከእቅድ በላይ ተሳክቷል ብለዋል።

በዚህም በተያዘው የመኸር ወቅት 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 6 ነጥብ 3 ሄክታር መከናወኑን ገልጸዋል።

ይህ ስኬት እንዳለ ሆኖ በመሰረተ ልማት በኩል ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ አለመጠናቀቃቸው እንደ ጉድለት የሚታዩ ሲሆን፣ በቀጣይ ስድስት ወራት የማካካሻ እቅድ ተይዞ  ይሰራል ብለዋል።

በክልሉ በመንግስት የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት በኩል የሚታዩ ችግሮች ተግዳሮት ሆነው መቆየታቸው በመድረኩ ተጠቁሟል።

መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ቀናት ይካሄዳል።