በመተከል ዞን ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው አካላት እየተፈጸሙ ያለውን የዜጎች ግድያና መፈናቀል መንግስት ሊያስቆም ይገባል – ምክር ቤቱ

399

አዲስ አበባ፣ ጥር 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ባላቸው አካላት እየተፈፀመ ያለውን የዜጎች ግድያና መፈናቀል ችግር በመንግስት ሊፈታ እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ በውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች እንዲሁም የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞንና በሌሎች አካባቢዎች የተፈጸመውን የዜጎች ግድያ አስመልክቶ በቀረበለት የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቷል።

ቋሚ ኮሚቴዎቹ በምርመራ ሂደታቸው ከደረሱባቸው ዋና ዋና ጭብጦች መካከል በመተከል ዞንና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰተው የጸጥታ ችግር ማንነትን መሰረት ያደረገ የንጹሃን ዜጎች ህይወት መቀጠፉን፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መድረሱን ጠቅሰዋል።

የተፈጠረው ችግር የተወሳሰበና በፍጥነት ሊገታ ያልቻለው የፖለቲካ ዓላማ ባላቸው አካላት ስለመሆኑ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ አስረድተዋል።

ህገ-መንግስታዊ መብትን ጥያቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሲነዛ የነበረው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ በህዝቦች መካከል ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን በሚሰብኩ የፖለቲካ ፍላጎት ባላቸው የውስጥና የውጭ የጥፋት ሃይሎች መሆኑንም አንስተዋል።

እንደ ዶክተር ነገሪ ገለጻ፤ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት የዴሞክራሲ ምህዳርን ለማስፋት አሳሪ ሕጎችን የማሻሻልና አዳዲስ ሕግጎችን በማውጣት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት አድርጓል።

ለውጡ ያልተዋጠላቸው የጥፋት ሃይሎች ግን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ለሚፈጠሩ ግጭቶችና ለንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፍ ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል።

በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከጥፋት ሃይል ጋር በማበር ችግሩ እንዲባባስ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በሚኒስትሮች ምክር ቤት የወጣውና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀውን የትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጻሚነት ወሰን ማስፋትና ማጥበብ እንደሚቻል መደንገጉን በመጥቀስ አዋጁን በመተከል ዞን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ አባላት ቋሚ ኮሚቴዎቹ ካነሷቸው የውሳኔ ሃሳቦች በተጨማሪ መፍትሄ ያሏቸውን ሌሎች ሃሳቦች አንስተዋል።

በተለይም ችግሩን በመፍጠር ረገድ እጃቸው ያለባቸውን የአመራር አካላት መረብ መበጠስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ሌላው ጁንታው ቀደም ብሎ የሰራቸውን የሴራ ተግባራት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊያከሽፋቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን የዜጎች መፈናቀልና የንብረት ውድመት በአስቸኳይ ስለሚቆምበት ሁኔታና ተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ ከምክር ቤቱ በተወጣጡ አባላት ቡድን እንዲቋቋም ቋሚ ኮሚቴዎቹ የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል።