የአውሮፓ ህብረት 800 ሺህ ዩሮ የሚያወጡ ሁለት የእንስሳት ክትባት ማምረቻ ማሽኖችን ድጋፍ አደረገ

1112

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2013(ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት 800 ሺህ ዩሮ የሚያወጡ ሁለት የእንስሳት ክትባት ማምረቻ ማሽኖችን ድጋፍ አደረገ። 

የአውሮፓ ህብረት ድጋፉን ያደረገው በዓለም የምግብ እና  እርሻ ድርጅት (FAO) በኩል ሲሆን የድጋፍ ስነስርዓቱ በቢሾፍቱ በሚገኘው ብሄራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ተከናውኗል።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና አሳ ሀብት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ  ከአውሮፓ ህብረት ልዑክ መሪ አምባሳደር ጆሃን ቦርግስታም እና በኢትዮጵያ የፋኦ ተወካይ ፋጡማ ሰዒድ ድጋፉን ተቀብለዋል።

ድጋፉ በአውሮፓ ህብረት፣ በዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት እንዲሁም በብሔራዊ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት እና በግብርና ሚኒስቴር መካከል በትብብር  ከ8 ዓመት በፊት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ፕሮጀክት አካል ነው።

ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ አርብቶ አደር አካባቢዎች የተሻለ የእንስሳት ጤና አገልግሎት አቅርቦትን በማቅረብ የአርብቶ አደሮች ህይወትን መቀየር ዓላማ ያደረገ ነው።

ፕሮጀክቱ የእንስሳት ጤና አገልግሎቶችን በመደገፍ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ እና የአርብቶ አደሮች ህይወት እንዲሻሻል አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስለመሆኑ ተጠቁሟል።

የአሁኑ ሁለቱ የእንስሳት ክትባት ማምረቻ ማሽን ድጋፍ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የእንስሳት ክትባት እጥረት ለሟሟላት ያግዛል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

በድጋፍ የተበረከተው ማሽን 22 የክትባት አይነቶችን በጥራት፣በብዛት እና በፍጥነት ማምረት ይጀምራል ብለዋል።

ይህም አገሪቱ በእንስሳት ሀብት ያላትን አቅም የእንስሳትን ጤና በማስጠበቅ በሚፈለገው መጠን ምርትና ምርታማነትን ለማስጠበቅ እንደሚረዳ ነው የተናገሩት።