በምንጃር ሸንኮራ 44 ታቦታት ከደብራቸው ወጥተው የሚከበረውን የጥምቀት በዓል የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መሰራት እንዳለበት ተጠቆመ

203

ጥር 13/2013(ኢዜአ) በምንጃር ሸንኮራ 44 ታቦታት ከደብራቸው ወጥተው የሚከበረውን የጥምቀት በዓል የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ለአካባቢው መሰረተ ልማትን ከሟሟላት ጀምሮ የማስተዋወቅ ስራ በስፋት ሊሰራ እንደሚገባ ተጠቆመ። 

በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሚከበረው የከተራና የጥምቀት በዓል ልዩ ገጽታ ያለው ነው።

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚጠቁመው የጥምቀት በዓሉ ከዛሬ 600 ዓመት በፊት በወረዳው ኢራንቡቲ ቀበሌ መከበር ጀምሯል።   

የጥምቀት ከተራ ላይም 44 ታቦታት ከደብራቸው ወጥተው ከ18 እስከ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ወዳለው የታቦት ማደሪያ መጥተው ከተራና ጥምቀት ይከበራል።

በዓሉ ሲከበርም ልዩ ድባብ ኖሮት በደማቅ ሁኔታ በየዓመቱ የሚከበር መሆኑ ይገለፃል።   

የኢዜአ ሪፖርተር በስፍራው ተገኝቶ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎች 44 ታቦታት ከደብራቸው ወጥተው የሚከበረውን የጥምቀት በዓል የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መስራት ይገባል ብለዋል።

ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የመጡት ዶክተር ክበበ ጸሃይ በሰጡት አስተያየት በዓሉ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ የሚከበርና ሳቢና ልዩ ገጽታ ያለው ነው።     

       

በስፍራው የሚከበረውን ክብረ በዓል የቱሪስት መስህብ ለማድረግ የጎብኚዎች ማረፊያ፣ መንገድና ሌሎችም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች መሟላት አለባቸው ንወ ያሉት።

በተለይም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጥናት በማድረግ ክፍተቱን የመለየት ስራ መስራት እንደሚኖርባቸው ጠቁመው ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው ብለዋል።  

የወረዳው መንገድና ትራንስፖርት ኃላፊ አቶ ወንዱ ጌታቸው፤ በምንጃር ሸንኮራ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ሁሉም ሊያየው የሚገባ ድንቅ ኩነት መሆኑን ገልጸዋል።

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዋልተንጉስ ዘርጋው በበኩላቸው በዓሉ ከ600 ዓመት በፊት መከበር የጀመረበት ቦታ ታሪካዊ ቢሆንም በዚህ ልክ እየተጎበኘ አይደለም ይላሉ።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ በበቂ ሁኔታ አለመተዋወቁን ነው ያብራሩት።

ቦታውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የሚጎሉ ነገሮችን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው አጥር የማሳጠርና የመጠመቂያ ገንዳ ለማሰራት ዲዛይን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም