በገላና ወረዳ 59 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው ሪፈራል ሆስፒታል በመገባደድ ላይ ነው

59

ነገሌ፣ ጥር 13/2013(ኢዜአ) በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ ለማድረግ 59 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ እየተገነባ ያለው ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ  80 በመቶ መድረሱ  ተገለጸ፡፡ 

በወረዳው ቶሬ ከተማ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስና የጤና ተቋም አገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል በሚቻልበት ዙሪያ  ውይይት ተካሂዷል፡፡ 


ውይይቱን የመሩት የወረዳው ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ በዳሳ ጂሎ እንዳሉት 150 ሺህ ህዝብ ለሚሆነው የወረዳው ነዋሪ በ15 የጤና ተቋማት እየተሰጠ ያለው አገልግሎት በቂ አይደለም፡፡

እናቶች በግንዛቤ ጉድለት ከጤና ተቋም ይልቅ በቤት ውስጥ መውለድን ስለሚመርጡ ለስነ ልቦናና አካል ጉዳት፤ ህጻናቱም ለሞት እየተጋለጡ ነው ብለዋል፡፡ 

ጉዳቱን ለመቀነስና የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማዳረስ  የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት እያከናወናቸው ካሉት ተግባራት መካከል  59 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የጀመረው ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ 80 በመቶ መጠናቀቁን ጠቅሰዋል።

በወረዳው ቶሬ ከተማ  በ2011 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይሄው ሆስፒታል የመኝታ፣ መድሃኒት፣ ቤተ-ሙከራና   ሌሎችን የህክምና መገልገያ ክፍሎችን አካቶ ከ100 ሺህ በላይ ህዝብንም ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

ይህም በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር 80 በመቶ ለማድረስና የህጻናትን ሞት ለመቀነሰ የጎላ  አስተዋጽኦ እንደሚኖረው  አቶ በዳሳ ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሳፋዬ ዲዶ በሰጡት አስተያየት በወረዳው  ሆስፒታል አለመኖርና የግንዛቤ ጉድለት በተለይም ሴቶች የሚያጋጥማቸው ችግር ከባድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ብርሀኔ ሸጦ በበኩላቸው በቤት ውስጥ ስንወልድ ብዙ ደም እንደሚፈሰንና ለችግር እንደምንጋለጥ ብናውቅም በቅርብ ሆስፒታል ባለመኖሩ ለጉዳት እንዳረጋለን ብለዋል፡፡


መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ያስጀመረው ሆስፒታል  ፈጥኖ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንዲበቃ ትኩረት እንዲሰጥ የሚፈልጉ መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከአካባቢው የተውጣጡ ነዋሪዎችና የጤና  ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም