ዳያስፖራው ድጋፍና አብሮነቱን ለማሳየት ለገበታ ለአገር 27 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል -

73

አዲስ አበባ፣ ጥር 13/2013(ኢዜአ)  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ድጋፍና አብሮነታቸውን ለማሳየት ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት 27 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል በቀጣይ ሳምንት በሚዘጋጀው የእራት መርሃ ግብር ላይ እንዲሳተፉ እጣ የወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ዝርዝርም ይፋ ሆኗል።

በብሔራዊ ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የውጭ ድጋፍ አሰባሳቢ ንኡስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎች ለሚገነቡት ፕሮጀክቶች ዳያስፖራው በተለያየ መልኩ ድጋፍ እያደረገ ነው።

"ለኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ዳያስፖራው ድጋፉንና አብሮነቱን እያሳየ ነው" ብለዋል።

በዚህ አመት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመላው አለም ከሚገኘው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ለገበታ ለአገር ፕሮጀክት 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን አብራርተዋል።

በሁለተኛው ሩብ አመት ለመሰብሰብ ከታቀደው 15 ሚሊዮን ብር 27 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ ድጋፉን ኢትዮጵያ ውስጥ በተከፈተው አካውንት፣ በሚሲዮኖችና ዳያስፖራው በግል፣ በቡድን፣ በማህበርና በድርጅት ስም ለፕሮጀክቱ ገቢ አድርጓል።

በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ልማት ለመሳተፍ እያሳዩ ያለውን ተነሳሽነት በመጠቀም በቀሪው ጊዜ ተጨማሪ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በቀጣይ ሳምንት በሚካሄደው የገበታ ለአገር የእራት መርሃ ግብር ላይ አስተዋጽኦ ካደረጉት መካከል ከአፍሪካ፣ ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓና መካከለኛው ምስራቅና ከሌሎች አካከባቢዎች እጣ የወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ተሳታፊ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

እጣ የወጣላቸው የዳያስፖራ አባላት አቶ የማነ በርሔ ወልደስላሴ፣ አቶ ዳንኤል በርሔ ወልደስላሴና አቶ መርሃዊ መስፍን ተስፋስላሴ ከአፍሪካ ደቡብ ሱዳን ናቸው።

በተመሳሳይ አቪያ ሆልዲንግስ ኮርፖሬሽን፣ ሶፊያ ዘውዱ አበራና አቶ አልታየወርቅ ብርሃነ ስላሴ ከሰሜን አሜሪካ ዩናይትድስቴትስ እጣ የወጣላቸው ናቸው።

ከአውሮፓ ጄኔቫ ደግሞ አቶ ረሻድ ከማል ጎበና እንዲሁም ከብራሰልስ ወይዘሮ ተዘራሽ ሽፈራው፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስራኤል አቶ ሙሉጌታ ገብሩ ይሳተፋሉ።

ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች አቶ አብዱልናስር ሃሮና ሻለቃ ጥሩነህ አላምረው እጣ ከወጣላቸው 11 የዳያስፖራ አባላት ውስጥ በመሆናቸው በመርሃ ግብሩ ይሳተፋሉ።

ዳያስፖራው ለህዳሴ ግድብ፣ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝና ለተለያዩ ሰብአዊ እርዳታና ኢትዮጵያን ለማልማት መንግስት በሚቀርጻቸው ፕሮጀክቶች ዳያስፖራው በእውቀት፣ በገንዘብና በሌሎች ተነሳሽነቱ መጨመሩን ገልጸዋል።

የዳያስፖራ አባላቱ ድጋፍ ለቤተሰብ፣ ለልጅና ለአገር ቋሚ ቅርስ ጥሎ የሚያቆይ በመሆኑ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፉን እንዲቀጥሉ አምባሳደር ብርቱካን ጥሪ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኒሼቲቭ የሆኑትን ኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪ ፕሮጀክቶች ስራ ለማስጀመር የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ ኢትዮጵያውያን እየተሳተፉ እንደሆነ ይታወቃል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም