የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ለጥናት የሚሆኑ ሰነድና ቅርሶችን ተረከበ

218

አዲስ አበባ፤ ጥር 13/2013(ኢዜአ)  የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በስጦታ ያገኛቸውን ለጥናት የሚሆኑ ሰነዶች እና ቅርሶችን ከበጎ ፈቃደኞች ተረክቧል። 

ባለስልጣኑ ቅርሶችን ከሚሰበስብባቸው መንገዶች አንዱ ከበጎ አድራጊዎች የሚበረከቱ ስጦታዎች መሆኑ ተገልጿል።

በበጎ አድራጊ ግለሰቦች የተሰጡ ስጦታዎችም የአርኪዮሎጂና ፖሊዮአንትሮፖሎጂ የጥናት ሰነዶች ፣ የኢትኖግራፊ ቅርሶች፣ የስእል ስራዎች እና በርካታ መጻሀፍት ናቸው።

ከነዚህም 400 በላይ መጻህፍትና 355 የኢትኖግራፊ ቅርሶች ይገኙበታል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ስጦታው ትውልድን በማነጽ እና ትውልድን በመገንባት ሂደት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ።

በርካታ ቅርሶች በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ የገለጹት ዶከተር ሙሉጌታ ህብረተሰቡ እነዚህን ቅርሶች ወደ ተቋሙ በማምጣት በክብር ተቀምጠው ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሻገሩ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

ባለስልጣኑ ቅርሶችን የመንከባከብ፣ የመጠበቅ እና የማልማት ስልጣን እንዳለው ጠቁመው በስጦታ የተሰጡት ቅርሶችና የጥናት ሰነዶች በተገቢው መንገድ ተይዘው ትውልድ እንዲማርባቸው ይደረጋል ብለዋል።

በቀጣይም ሰነዶቹን በማደራጀትና ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች በግብአትነት እንዲያገለግሉ ለዘርፉ ተጠቃሚዎች በተደራጀ መልኩ እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።

በባለስልጣኑ የቅርስ ማሰባሰብ ማደራጀትና የላቦራቶሪ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም አማረ ቅርሶቹ በዚህ ቦታ መቀመጣቸው ለጥበቃ ፣ ለጥገና እና እንክብካቤ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

በቀጣይም ቅርሶቹ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለኤግዚቢሽን እንዲውሉ የሚሰራ ይሆናል ብለዋል።

ህብረተሰቡም መሰል ተግባራትን በማድረግ በቅርሶች ላይ የሚደርሰውን ዝርፊያና ጉዳት ሊከላከል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ቅርሶች በግለሰብ እጅ እንዳይያዙ ባይከለከልም ነገር ግን ወደ መሰል ተቋማት የማምጣት ነገር ሊለመድ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በርክክቡ ላይ ስጦታውን ለሰጡ አራት ግለሰቦች የእውቅና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም