ፍርድ ቤቱ በግጭት የተጠረጠሩ ተጨማሪ ግለሰቦችን ጉዳይ ተመለከተ

51
አሶሳ ሀምሌ17/2010 የአሶሳ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዞኑ ሸርቆሌ ወረዳ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር የተጠረጠሩ ተጨማሪ አስር ግለሰቦችን  ጉዳይ ተመለከተ። ፍርድ ቤቱ ትላንት ጉዳያቸውን የተመለከተው ግለሰቦች  ሰኔ 17 ቀን 2010 ዓ.ም ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር የንፁሃንን ህይወት በማጥፋት፣ የአካል ጉዳት በማድረስና ንብረት በማውደም ወንጀሎች የተጠረጠሩ ናቸው፡፡ ይሁንና ጉዳዩን እንዲከታተል የተዋቀረው የምርመራ ቡድን ምርመራውን በሰውና በሰነድ ማስረጃ አስደግፎ ለማቅረብ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡ በዚሁ መሰረት የፍርድ ቤቱ ሁለተኛ ምድብ የወንጀል ችሎት ጥያቄውን በመቀበል የክስ መዝገቡን ሃምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ለመመልከት ቀጥሯል ። በክልሉ በአሶሳ ከተማ፣ በሸርቆሌ ወረዳና በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳዎች ተከስቶ በነበረ የፀጥታ ችግር ተጠርጥረው በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ቁጥር 108 መድረሱ ታውቋል ፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም