የኦነግ ሸኔ አባላት ከነትጥቃቸው በቁጥጥር ሥር ዋሉ

311

ሐረር፤ ጥር 12/2013 (ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በጥምቀት በዓል ላይ ሽብር ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሶስት የኦነግ ሸኔ አባላት ከነ-ትጥቃቸው በቁጥጥር ስር ማዋሉን የሀገር መከላከያ ምስራቅ ዕዝ አስታወቀ።

የዕዙ የሰብአዊ መረጃ ሃላፊ ኮረኔል ደቻሳ ጅማ እንደገለጹት በክብረ በዓሉ ላይ አደጋ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ የቡድን መሪውን ጨምሮ ሶስት የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል።

የጸጥታ አካላትና ማህበረሰቡ ባከናወኑት የተቀናጀ ሥራ ታጣቂዎቹ በክልሉ ድሬ ጠያራ ወረዳ ምንም ዓይነት ጥፋት ሳይፈጽሙ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏልም ብለዋል።ለጥፋት ዓላማቸው ሊጠቀሙበት የነበሩ ሁለት ክላሽንኮቭ እና ሁለት ቦንብ እንዲሁም አንድ ሽጉጥ በቁጥጥር ሥር መዋሉም ኮረኔል ደቻስ አስታውቀዋል።

በሐረር ፣ሐረማያ፣ አወዳይ እና ድሬዳዋ ከተሞች ላይ ማዕከል በማድረግ ሊፈጸም የነበረው ጥቃትም መክሸፉን ነው ያስረዱት።እንደ ኮረኔል ደቻሳ ገለጻ ቀሪ አለ የተባሉ የኦነግ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የጸጥታ ሃይሉ ክትትል እያደረገ ነው።

ኮረኔል ደቻሳ እንዳመለከቱት ከምስራቅ ሐረረርጌ ዞን ደደር እና መልካ በሎ ወረዳ ተነስተው ጥፋት ለመፈጸም ሲዘጋጁ የነበሩና በቁጥጥር ሥር የዋሉት ታጣቂዎች ኢብሳ ሼህ መሐመድ፣ አህመድ መሐመድ እና ዮስፍ አህመድ ናቸው።

ህብረተሰብም ከጸጥታ አካላቱ ጋር ህግ ለማስከበር እየሰጠ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።