የሱዳን ጦር ድንበር አልፎ መሬት እንዲይዝ በኢትዮጵያ አመራር እንደተነገረ የሚነዛው ወሬ ፍፁም ሀሰት ነው- አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

105

አዲስ አበባ ጥር 12/2013 (ኢዜአ) የሱዳን ጦር ድንበር አልፎ መሬት እንዲይዝ በኢትዮጵያ አመራር እንደተነገረ የሚነዛው ወሬ ፍፁም ሀሰት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

አምባሳደር ዲና በዛሬው እለት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ወዳጅነት ጥልቀት ያለው መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለሱዳን ሰላምና መረጋጋት ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰው የቅርብ ጊዜውን የኢትዮጵያ መሪዎች ጥረትም ለአብነት አንስተዋል። 

ኢትዮጵያ በትግራይ ህግ ማስከበር ላይ በነበረችበት ጊዜ የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት ታሳቢ በማድረግ ወንጀለኞች ወደ ሱዳን እንዳይገቡ በኢትዮጵያ በኩል እንደተነገራት ገልፀው፣ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው ብለዋል። 

የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ መሬት መያዙ ሳያንስ ከኢትዮጵያ ግዛት አልወጣም የሚል ንግግር እየተሰማ መሆኑን ገልፀዋል። 

በኢትዮጵያ መሪዎች በኩል ከ100 ዓመት በላይ የሆነውን ኢትዮጵያን መሬት ገብታ እንድትይዝ እንደተነገረ በተለያዩ ሚዲያዎች የሚነዛው ወሬም ፍፁም ሃሰት መሆኑን ገልጸዋል።

"ይህ ሊሆንም አይችልም፣ አልሆነም፤ ቅዠት ነው" ሲሉ አምባሳደር ዲና አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አቋም አሁንም ቢሆን ወደ ቀደመው የድንበር ድርድር መሆኑንም ገልጸዋል። 

በሌላ በኩል በሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራና ሶማሊያ ወታደሮች እንደገቡ የሚራገበው ወሬም ከእውነት የራቀ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህን የፈጠራ ወሬ የሚያራግቡ ህግ ማስከበሩን ቀጣናዊ ችግር ለማድረግ የሚሹ ኃይሎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም