በአፋር ክልል የበረሀ አንበጣ ደግም ተከሰተ

81

ሰመራ፤ ጥር12/2013 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የበረሃ አንበጣ ዳግም መከሰቱን የክልሉ እርሻ፣ አርብቶ አደርና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የበረሃ አንበጣ መከላከል ግብረ-ሃይል አስተባባሪ ዶክተር አያሌው  ሹመት ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ አፋምቦ፣ ዱብቲና አይሳኢታ ወረዳዎች ጥር 9 ቀን 2013 ዓ.ም የአንበጣ መንጋው ዳግም ተከስቷል።

መነሻውን ከጅቡቲና ሱማሌ ያደረገው የአንበጣ መንጋ በሌሎችም የክልሉ ወረዳዎች እየተስፋፋ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ሚሌ፣ ጭፍራ፣ ጉሊናና ቴሩ ወረዳዎች የአንበጣ መንጋው የተስፋፋባቸው መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ  በክልሉ የግብርና ስራዎች የሚከናወኑበት ወቅት በመሆኑ የአንበጣ መንጋው ከእንስሳት መኖ በተጨማሪ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ህብረተሰቡን በማሳተፍ  በባህላዊ መንገድ የመከላከል ስራ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

መንጋው እስካሁን ያደረሠውን ጉዳት ለማወቅ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑንም ገልጸው፤ መንጋውን ለመቆጣጠር በሰውና በተሽከርካሪ ኬሚካል ለመርጨት አስቸጋተሪ በመሆኑ  አካባቢዎች ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት ለማካሄድ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስተባባሪው አስታውቀዋል።

በክልሉ ካለፉት ሁለት አመት ወዲህ በተደጋጋሚ የበረሃ አንበጣ ተከስቶ በሰብል፣ በእንስሳት መኖና ቁጥቋጦዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም