ፖሊስና ህብረተሰቡ እጅና ጓንት ሆኖ ከሰራ የማንወጣው የፀጥታ ችግር የለም… የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

87

አዲስ አበባ፤ ጥር 11/2013(ኢዜአ) ፖሊስና ህብረተሰቡ እጅና ጓንት ሆኖ ከሰራ የማንወጣው የፀጥታ ችግር የለም ሲል የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ ካስመዘገበቻቸው ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የሆነው የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም በከበሩን ኮሚሽኑ አስታወቀ።

የፌዴራል፣ የክልል፣ የአዲስ አበባና የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽኖች እንዲሁም የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ሌሎች የጸጥታና የፍትህ አካላት ሰላም ወዳዱን ህዝብ ከጎናቸው በማሰለፍ ባደረጉት ቅንጅታዊ የፀጥታ ስራ በዓሉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በመላው ሀገሪቱ  በሰላምና ድምቀት ተከብሮ መዋሉን ኮሚሽኑ ገልጿል።  

ኮሚሽኑ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ ፖሊስ ኮሚሽኖች ከባዓሉ ዋዜማ ጀምረው ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር የፀጥታውን ስራ በተቀናጀና በተዋሀደ አኳሃን በዕቅድ በመመራት የህዝቡን ፀጥታና ደህንነት የማስከበር ስራቸውን በብቃት ተወጥተዋል።

በጥበቃው ላይ የተሰማሩት የሰራዊቱ አባላትም ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ከራሳቸው በፊት የህዝቡን ደህንነት በማስቀደም የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት በመወጣት የታለመውን ግብ ማሳካታቸውም ነው የተገለጸው።

ለዚህ ስኬት ትልቁን ድርሻ የተወጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የየደብሩ አስተዳደሮች፣ የከተራና የጥምቀት በዓሉ አስስተባባሪዎች፣ ህዝበ ክርስቲያኖች እንዲሁም ወጣቶች ለጸጥታ አስከባሪ አካላት ያሳዩት ከፍተኛ ትብብር አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል።

በነገው ዕለትም የሚገቡ ታቦታትን በማጀብ ሂደት እንዲሁም ወደ ፊትም በተመሳሳይ በሀገሪቱ የሚከበሩ ታላላቅ በዓላት ላይም  ትብብሩ ሊቀጥል ይገባል ብሏል ኮሚሽኑ።

በዚህም የፌዴራል፣ የክልል፣ የአዲስ አበባና የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽኖች እንዲሁም ሌሎች የፀጥታ አካላት የላቀ ምስጋና ማቅረባቸውን በመግለጽ፤  እንደዛሬው ህዝብና ፖሊስ አብሮ ተባብሮ ከሰራ የማንሻገረው የሰላምና የደህንነት ችግር እንደሌለ እርግጠኞች ሆነናል ብሏል።

ከፖሊስ የተሰጠውን መግለጫ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ላደረጉት ሁሉ ኮሚሽኑ ምስጋና አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም