ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለሀገር ሠላምና ልማት በጋራ መስራትን ታሳቢ ሊያደርግ ይገባል..አቡነ ዮሴፍ

68

ሐዋሳ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለሀገር ሠላምና ልማት በጋራ መስራትን ታሳቢ ሊያደርግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀዻዻስ አቡነ ዮሴፍ አሳሰቡ።

የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በዚሁ ጊዜ ሊቀዻዻሱ ቡራኬና ቃለ ምዕዳን ከሰጡ በኋላ እንዳሉት በቅዱስ መፅሐፉ እንደተፃፈው ያለው ለሌለው በማካፈልና በመተዛዘን በዓሉን ሊያከብር ይገባል።

በተለይ ህዝበ ክርሰቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ከመለያየት ይልቅ ለአገር ሠላምና ልማት በጋራ መስራትን  ታሳቢ በማድርግ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በባዕሉ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የሐዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ በበኩላቸው በዓሉ ከመንፈሳዊ ገፅታው ባለፈ የማህበራዊና ባህላዊ ማንነት መገለጫ መሆኑን ገልፀዋል።

ክብረ በዓሉ ህዝበ ክርስቲያኑን ይበልጥ በማቀራረብ በጋራ የመኖር እሴቱን የሚያጎለብት ስለሆነ ምዕመናኑ ቱውፊቱን ለመጪው ትውልድ ሳይበረዝ ሊያስቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በባዓሉ ላይ የሀዋሳ ከተማና የሲዳማ ክልል የመንግስት ባለስልጣናት፣ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን በመታደም በጠበል ርጭት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተካፍለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም