የሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችንን ትውፊቶቻቸውን ጠብቀንና ተንከባክበን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን-- ዶክተር ሂሩት ካሳው

57

አዲስ አበባ ጥር 11/2013 (ኢዜአ) የሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቻችንን ትውፊቶቻቸውን ጠብቀንና ተንከባክበን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ተናገሩ።

ሚኒስትሯ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በመገኘት ንግግር አድርገዋል።

በመልእክታቸውም ጥምቀት በይቅርታና በፍቅር እንድንኖር፣ እርስ በርሳችን እንዲንተሳሰብ እንዲሁም ከጥፋት በመራቅ በአዲስ አስተሳሰብ ወደ ፊት እንድንመለከት የሚያደርግ ነው ብለዋል።

"ፈጣሪ ያለ ፈቅር አይገኝም" ያሉት ሚኒስትሯ "አንዳችን ለሌላችን በማሰብና በመቆርቆር፣ ተደጋግፈን በአብሮነታችን መዝለቅ አለብን" ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶቻችንንና ወላጆቻችንን ምክር በመስማት፣ ከክፋት በመራቅና ለመልካም ነገር በመዘጋጀትና በመስራት ልንዘልቅ ይገባልም ነው ያሉት።

ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ ለተከታይ ትውልድ ማስተላለፍም የአሁኑ ተውልድ ሃላፊነት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይ ወጣቶች ለአገራቸው መልካም ነገርን በመሰነቅ ለእድገት፣ ሰላምና ፍቅር እንዲሁም አብሮነት ጠበቃ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የጥምቀት ክብረ በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገበ አንድ ዓመት እንደሆነውም ሚኒስትሯ አስታውሰዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ባስተላለፉት መልእክት የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊነቱ በተጨማሪ ማህበራዊ ፋይዳውም የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ከውጭም ከአገር ወስጥም በርካቶች የሚታደሙበት ደማቅና ልዩ ድባብ ያለው በዓል መሆኑንም አንስተዋል።

ጥምቀት የኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የዓለም ቅርስ በመሆኑ ልንጠብቀውና ልንንከባከበው ይግባልም ነው ያሉት።

በጥምቀት ወስጥ ኢትዮጵያን እንመለከታታለን፣ ዥንጉርጉር መልክና ውበታችንም ጎልቶ የሚታይበት መሆኑን ምክትል ከንቲባዋ ገልጸዋል።

"ጠርዝ ለጠርዝ ቆመን አገር መገንባት፣ ፈጣሪን ማምለክ፣ በዓልን ማክበር አንችልም" ያሉት ምክትል ከንቲባዋ እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ ሰርገኛ ጤፍ ነን፤ ልንለያይ አንችልም፤ በመከባበር መቀራረብ አለብን ሲሉም መልአክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም