የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ዓለማቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል -- ብፁዕ አቡነ ማትያስ

119

ጥር 10/2013 (ኢዜአ) የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት መመዝገቡ ዓለማቀፋዊ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጎታል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ገለጹ።

የከተራ በዓል በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ዛሬ በጃንሜዳ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ የከተራና የጥምቀት በዓልን በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጥምቀት በዓል እየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቆ ሃጥያትን ያስወገደበት ታላቅ በዓል እንደሆነ ብፁዕነታቸው ገልጸዋል።

እየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቅ ትህትናውን ማሳየቱንና ዓለምን እንዳዳነ ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከምታከብራቸው አበይት በዓላት አንዱ ነው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዓሉ በሁሉም የእድሜ ክልል የሚገኝ የእምነቱ ተከታይ የሚያከብረው ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በዓሉ በ2012 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት መመዝገቡ ዓለም አቀፋዊ በዓል እንዳደረገውና የዓለምን ህዝብ ትኩረት እንዲስብ ማድረጉን አመልክተዋል።

ብዙ የውጭ አገር ጎብኚዎች የበዓሉን ስርዓት ለመመልከት እንደሚመጡና ባዩትም ነገር እንዲደነቁ የሚያደርጋቸው መሆኑን ነው ብፁዕነታቸው በመልዕክታቸው ላይ ያወሱት።

የከተራና የጥምቀት በዓል በአንድ ጊዜ ብዙ ሕዝብ በአንድ ቦታ የሚያከብረው የአደባባይ በዓል እንደሆነና በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለንን ጠንካራ እምነት የምናሳይበት መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝበ ምዕመኑ በዓሉን ከዚህ በበለጠ አንድነት፣ ፍቅርና ሕብረት ሊያከብረው እንደሚገባም አመልክተዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲከበር አስተዋጽኦ እያደረጉ ላሉ የጸጥታ አካላት ብፁዕ አቡነ ማትያስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስን ጨምሮ ብፁዓን አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የከተራ በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱ ከትርጓሜው የሚነሳ ነው፤ ከተራ ከተረ ከበበ ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ሲሆን ፍቺው መከተር መገደብ ማለት ነው።

የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውሃ ባላበት ቦታ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል።

ድንኳን ከሌለ ዳስ የሚጣል ሲሆን የምንጮች ውሃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል ጉድጓድ እየተቆፈረ ውሃው እንዳይሄድ ይገደባል።

ውሃው የሚከተረው በማግሥቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው።

የጥምቀት በዓል ነገ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም