የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር የባህል ፌስቲቫልና ሻምፒየና ውድድር በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አሽናፊነት ተጠናቀቀ

ደሴ፤ ጥር 10/2013 (ኢዜአ) የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን 14ኛው የባህል ፌስቲቫልና ሻምፒዮና ውድድር በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አጠቃላይ አሽናፊነት ተጠናቀቀ።

ከጥር 03 ቀን 2013 ጀምሮ በከሚሴ ከተማ ሲካሄድ ቆይቶ  ትናንት በተጠናቀቀው ውድድሩ በሁለቱም ፆታዎች ገበጣንና ትግልን ጨምሮ በስድስት የስፖርት ዓይነቶች 175 ስፖርተኞች ተሳትፈዋል፡፡

በውድድሩ ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አምስት ዋንጫዎችን በማግኘት አጠቃላይ አሸናፊ ሲሆን ከሚሴና ባቲ ከተሞች ደግሞ በቅደም ተከተል አራትና ሦስት ዋንጫዎችን በመውሰድ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል፡፡

የዞኑ ስፖርት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ ፀጋዬ በቀለ እንደገለጹት የውድድሩ ዓላማ በክልል ደረጃ በተያዘው ወር መጨረሻ በኮምቦልቻ ከተማ በሚካሄደው የባህል ፌስቲቫልና ሻምፒዮና ላይ ዞኑን የሚወክሉ ስፖርተኞችን ለመምረጥ የተካሄደ ነው፡፡

ውድድሩ የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር ብሎም የባህል ስፖርቶችን ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም ተናግረዋል። 

በውድድሩም ዞኑን ወክለው የሚሳተፉ 39 ስፖርተኞች መመረጣቸውንም አስታውቀዋል፡፡

ከባቲ ከተማ የመጣው የትግል ስፖርት ተወዳዳሪ ተሳታፊ ወጣት አህመድ ረታ በሰጠው አስተያየት ባደረገው ቅደመ ዝግጅት ተወዳድሮ በማሸነፍ ዞኑን ወክሎ ለመወዳደር መመረጡን ገልጿል። 

በቀጣይም በክልል ደረጃ በሚካሄደው ውድድር በትግል ስፖርት የተሻለ ውጤት ለማምጣት ዝግጅት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም