በኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ አዘገጃጀትና ሪፖርት ሥርዓት ለመተግበር የባለሙያዎች ትብብር ያስፈልጋል

105
አዲስ አበባ ሀምሌ 16/2010 አለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ አዘገጃጀትና ሪፖርት ሥርዓት ለመተግበር የዘርፉ ባለሙያዎች ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ገለጸ። አለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አስተማማኝ የፋይናንስ ሪፖርት በማቅረብ የአገሪቱን ኢንቨስትመንት ለማጎልበትና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ባለሙያዎች ሚና የጎላ እንደሆነ ተገልጿል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ባንኮችና ኢንሹራንስ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም በዓመት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያላቸው ድርጅቶች ዓለም አቀፍ መስፈርቱን ያሟላ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አዋጅ ቁጥር 847/2006 ማውጣቱ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ በአገሪቱ የተፈቀደላቸው የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲት ባለሙያዎች ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል። የቦርዱ ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ከ2 ሺህ በላይ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ባለሙያዎች አስተማማኝ የፋይናንስ አዘገጃጀትና ሪፖርት ለማቅረብ ሚናቸው የጎላ ነው። አለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሪፖርት ለማዘጋጀት ቦርዱ በሙያው የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ቢኖርበትም የሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች በኃላፊነት ከሰሩ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ባንኮችና መድህን ድርጅቶች፣  የመንግስት የልማት ድርጅቶች እንዲሁም በዓመት ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያላቸው ድርጅቶች አለም ዓቀፍ የፋይናንስ አዘገጃጀትና ሪፖርት እንዲያቀርቡ መመሪያው እንደሚያዝ ተናግረዋል። በዚህም ባንኮችና መድህን ድርጅቶች ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ህግ መሰረት ሪፖርት ማድረግ መጀመራቸውን ገልጸዋል። ቦርዱ በዓመት ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ያላቸው ድርጅቶችም እስከ 2012 ዓ.ም አለም አቀፍ መመሪያውን ተከትለው ሪፖርት እንዲያደርጉ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል። ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር በመዘርጋት የሚደርሰውን የሃብት ብክነት በመቀነስና ኢንቨስተሮችን በመሳብ የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል። የተፈቀደለት የሂሳብ አዋቂ አቶ ይርጉ ታምርና የኦዲት ባለሙያው አቶ ውዱ ተጫነ ለፋይናንስ አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት ኢትዮጵያ አለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ማቅረብ እንዳለባት ገልጸዋል። የአገሪቱን የፋይናንስ አዘገጃጀትና ሪፖርት ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ ከመንግስት ጎን በመቆም ሙያዊ ሃላፊነታቸውንና አገራዊ ግዴታቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል። ይህንን ግብ ለማሳካት ቦርዱ ለሂሳብ አዋቂዎችና ኦዲተሮች እንደሌሎች ሙያዎች አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልጸው፤ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ የተሰማሩ አካላትም ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በትብብር ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል። በአለም ላይ ደረጃውን የጠበቀ የፋይናንስ አዘገጃጀትና ሪፖርት የሚያቀርቡ አገሮች ከ148 በላይ ሲሆኑ ኢትዮጵያም አንዷ ለመሆን ወደ ሪፖርት ስርዓቱ እየገባች ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም