በጥምቀት ዋዜማ በተለያዩ ዲዛይኖች የሚዘጋጁ የባህል አልባሳት ግብይት ደርቷል-ነጋዴዎች

367

ጎንደር፣ ጥር 9/2013(ኢዜአ) በጥምቀት በአል በተለያዩ ዲዛይኖች ተዘጋጅተው ለሽያጭ የሚቀርቡ የባህል አልባሳት ምርቶች ትውልዱ ለባህላዊ አልባሳት ትኩረት እንዲሰጥ እያደረጉ መሆናቸውን በጎንደር ከተማ የባህል አልባሳት ተጠቃሚዎችና ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡

በከተማው የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች የጥምቀት በአልን ምክንያት በማድረግ ባህላዊ እሴቱን ሳይለቅ የተዘጋጁ የባህል አልባሳትን በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ መሆናቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ዘመኑን በሚመጥንና በሁሉም የእድሜ ደረጃ ተዘጋጅተው የሚሸጡ የባህል አልባሳት ወጣቱ በሀገሩ የባህል ልብሶች እንዲኮራና እንዲጠቀም ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ያለው ወጣት መኳንንት ሲሳይ ነው፡፡

ሴት ልጅ አምራና ደምቃ የምትታይበት እለት ቢኖር ጥምቀት ነው ያሉት ወይዘሮ እቴናት ሞላ በበኩላቸው ከፊትና ከኋላው በመስቀል ቅርጽ ተጠልፎ የሚዘጋጀው የጎንደር የባህል ቀሚስ በበአሉ ተፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። 

አቶ ጀምበሩ አይሸሹም የተባሉ የከተማው ነዋሪ በበኩላቸው የቀደምት አባቶቻችን የጀግንነትና የተጋድሎ ተምሳሌታዊ አለባበስ የሆነው የጃኖ ባህላዊ ልብስ በጥምቀት እለት የባህል ማድመቂያ ከሆኑ ባህላዊ አልባሳት አንዱ ነው ብለዋል፡፡

ትውልዱ ባህሉና እምነቱንና የቀደምት አባቶቹን የአለባበስ ስርአት ጠብቆ በማቆየት ረገድ ጥምቀትን የመሳሰሉ ሃይማኖታዊ በአላት የጎላ ሚና እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ 

የወጣቱን የጎልማሳውን የአዛውንቱንና የወይዛዝርቱን የአለባበስ ስርአት ጠብቀው የሚዘጋጁ የባህል አልባሳት ከጊዜ ወደ ጊዜ በአይነትም በብዛትም እየጨመሩ መጥተዋል ያሉት ደግሞ የባህል አልባሳት ነጋዴዋ ወይዘሮ ፋጤ ያሲን ናቸው፡፡

በጎንደር አካባቢ በስፋት የሚዘወተረው የጎንደር የባህል ቀሚስ በዘንድሮ የጥምቀት በአል ተፈላጊነቱ መጨመሩን የተናገሩት ወይዘሮዋ እስከ 1ሺ 200 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሌላው የባህል አልባሳት ነጋዴ አቶ ሲራጅ መሀመድ በበኩላቸው በወርሃ ጥር፤ ጥምቀት ብቻ ሳይሆን ጋብቻ ፈጻሚ ጥንዶችም የባህል አልባሳት ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከ2ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 8ሺ ብር የሚሸጥ የባህል አልባሳት መኖሩን ጠቁመው ጥምቀት ላይ የሚታደሙና በሰርግ የሚዳሩ ሙሽሮችም ምርቶቻቸውን በስፋት እየገዙዋቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በጎንደር በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርአት በሚከበረው የጥምቀት በአል በርካታ የከተማው ነዋሪዎች በበአሉ የሚታደሙ ሲሆን በነገው እለትም የዋናው በአል አካል የሆነው የከተራ በአል በድምቀት ይከበራል፡፡