የከተራና ጥምቀት በአል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት መደረጉ ተነገረ

135

ድሬዳዋ /ሀዋሳ/ ሶዶ/ መተማ ጥር 9/2013 (ኢዜአ)- በድሬዳዋ፣ ሀዋሳ ፣ ወላይታ ሶዶና በምእራብ ጎንደር ዞን የከተራና ጥምቀት በአል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት መደረጉን ፖሊስና የአስተዳደር አካላት አስታወቁ።

የድሬዳዋ የፖሊስ ኮሚሽን የለውጥ ስራዎችና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻለ ኢዜአ እንደገለጹት ፖሊስ ከህብረተሰቡና ከሀይማኖት አባቶች ጋር ተወያይቶ በአላቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር በድምቀት እንዲከበሩ ለማድረግ ዝግጅት አጠናቋል።

የጸጥታ ማስከበር ስራው በድሬደዋና በፌደራል ፖሊስ ቅንጅት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።

በጸጥታ ማስከበር ስራው በየቀበሌውና በየአካባቢው የተደራጁ ወጣቶችም ተሳታፊ እንደሚሆኑ  አመልክተዋል።

በተመሳሳይ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል ካለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ሁሉንም የፀጥታና የሚመለከታቸው አካላትን ያሳተፈ ግብረ ሃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።

ግብረ ሀይሉ የጸጥታ ሃይሎች፣ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የዕምነት አባቶችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓሉ በድምቀት እንዲከበር ከተማዋን የማጽዳትና የማስዋብ ሥራ በወጣቶች እየተካሄደ እንደሆነም አመልክተዋል።

"በየክፍለ ከተማ ከሚገኙ የወጣት አደረጃጀቶች በአሉ በሰላም እንዲከበር ከጸጥታ ሀይሉ ጋር በጋራ እየሰሩ ነው ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ መኩሪያ መኒሳ ናቸው።

ወደ ሐዋሳ ከተማ የሚመጡ እንግዶች ካለምንም ስጋት ከተማዋን ጎብኝተው እንዲወጡ የተቀናጀ የጸጥታ የማስከበር ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የጥምቀት በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር ለማስቻል ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የገለጸው ደግሞ የሶዶ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ነው።

ከከተራ ጀምሮ በዓሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ መከናወን በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ ከሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት ጋር በመወያየት በየአካባቢው ምደባ መደረጉን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ካሳሁን በሊላ አስታውቀዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ በበኩሉ የከተራና የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ለማድረግ 2 ሺህ 500 ሰላም አስከባሪ ወጣቶች መዘጋጀታቸውን  አስታውቋል።

የመምሪያው ተወካይ ኃላፊና የማህበረሰብ አቀፍ ወንጀል መከላከል ዋና ክፍል ኃላፈ ዋና ኢንስፔክተር ሐይማኖት ከፋለ ለኢዜአ እንደገለፁት ሃይማኖታዊ በዓሉን ያለምንም የፀጥታ ችግር ለማክበር ዝግጅት ተደርጓል።

ለዚህም ዞናዊ የሆኑ የፀጥታ ስጋቶችን በመለየትና ወጣቶችን ከፀጥታ አካላት ጋር በማቀናጀት ተገቢው ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

የሰላም ማስከበር ስራውን ከፀጥታ ሃይሉ ጎን ሆነው ለሚያግዙ ወጣቶች የደረት ባጅና ዩኒፎርም መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ወጣቶቹ በሰፈር አደረጃጀት እንደተሰራላቸውና ቀልጣፋና ውጤታማ የመረጃ ቅብብል እንዲኖር የቡድን መሪና አስተባባሪ ተመርጦ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም