ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የታቦት ማደሪያ ስፍራ አፀዱ

500

አዲስ አበባ፣ ጥር 9 / 2013 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ የታቦት ማደሪያ ስፍራ አፀዱ።

ምክትል ከንቲባዋ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኝ የታቦት ማደሪያ ከተለያዩ እምነት ተከታይ አባቶችና ምእመናን ጋር በመሆን ፅዳት አከናውነዋል።

ፅዳቱን ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አካባቢ በመገኘት ያከናወኑ ሲሆን “የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ፋይዳው ባሻገር ማህበራዊ ጥቅሙም ትልቅ ነው” ሲሉ ተናግረዋል ምክትል ከንቲባዋ።

የጥምቀት በዓል የኢትዮጵያዊያን ህብር የሚገለፅበት ልዩ ድምቀት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የጋራ የፅዳት መርሃ ግብሩ ኢትዮጵያዊያን የተለያየ ሃይማኖት፣ ብሄርና ማንንት ቢኖራቸውም አንድ መሆናቸውን ያመላከተ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሃይማኖት አባቶቹም በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት “ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም በጋራ መስራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን” ብለዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላምና ደህንነት ከመቸውም ጊዜ በላይ በጋራ እንዲቆሙ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።