ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር ያለበትን ቦታ እንዲለቅ በመጠየቁ የሚደግፋቸው ወገኖች አደጋ ላይ ወድቀዋል

139

ጥር 8/2013 (ኢዜአ) ሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር በኪራይ አገልግሎት የሚሰጥበትን ቦታ እንዲለቅ በመጠየቁ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ወገኖች አደጋ ላይ መውደቃቸውን አስታወቀ።

በቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩባ ለማኅበሩ ስራ የተፈቀደው ቦታ ጉዳይ መፍትሔ አለማግኘቱንም ገልጿል።

የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር የሚገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የማኅበሩ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሙዳይ ምትኩ ማኅበሩ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሕጻናት፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

እነዚህን ወገኖች ከልመና፣ ከጎዳና ኑሮና ከሴተኛ አዳሪነት ሕይወት በማውጣት ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ ዓላማ ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ማኅበሩ ከ650 በላይ ሕጻናትና 450 እናቶችን መጠለያ በመከራየት ምግብ፣ አልባሳትና የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገም ነው።

ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱትን ባሰራው ትምህርት ቤት በማስተማር፣ በሌሎች የትምህርት ደረጃዎች የሚገኙትን ወጪያቸውን ሸፍኖ እያስተማረ እንደሚገኝ ነው ነው ወይዘሮ ሙዳይ ያስረዱት።

እናቶቹ ከተረጂነት እንዲወጡ በሽመና፣ በሸክላ፣ በስፌትና በሌሎች ሙያዎች በማሰልጠን የራሳቸው ገቢ እንዲኖራቸው እያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

ማኅበሩ እነዚህን ተግባራት የሚያከናውነው ያለ ምንም የውጭ አገር ቋሚ ፈንድ ሲሆን በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ተቋማት እንደሚደግፉት አስረድተዋል።

ማኅበሩ ስራዎቹን የሚያከናውነው ተከራይቶ በወር 160 ሺህ ብር በሚከፍልበት ቤት እንደሆነም ገልፀዋል።

ይሁንና አከራዮቹ ቤቱን ለሌላ ስራ በመፈለጋቸው እስከ ሰኔ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ቦታውን እንዲለቅ የጊዜ ገደብ የተሰጠው በመሆኑ የሚደግፋቸው ወገኖች ላይ አደጋ መደቀኑን የገለጹት ወይዘሮ ሙዳይ የመንግስትና የሚመለከታቸውን አካላት ድጋፍ ጠይቀዋል።

የማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ታደለ አየለ በበኩላቸው ማኅበሩ በኪራይ ምክንያት መቸገሩንና ድጋፍ እንደሚሻ ለቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ማሳወቃቸውን ያወሳሉ።

አቶ ድሪባ የማኅበሩን ችግር በመረዳት አምስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ እንዲፈቀድለት መመሪያ መስጠታቸውን ሆኖም መመሪያው ተፈጻሚ ሳይሆን በኢንጂነር ታከለ ኡማ መተካታቸውን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ጉዳይ፣ የፋይናንስ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮዎች ማኅበሩ የተፈቀደው ቦታ ይገባዋል አይገባውም የሚለውን በተናጠል በመምጣት መገምገማቸውንም ተናግረዋል።

ቢሮዎቹ በግምገማቸው ቦታው እንደሚገባውና መሬቱን ቢያገኝ አሁን ካለበት የተሻለ ስራ መስራት ይችላል በሚል ጉዳዩን ለከተማው መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ መምራታቸውን አስረድተዋል።

መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮም ቦታው እንዲሰጠው ለየካ ክፍለከተማ ጥያቄ ቢያቀርብም ክፍለ ከተማው በአንድ ጊዜ 5 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማግኘት አልችልም በማለት ሐያት መኖሪያ መንደር ጀርባ 3 ሺህ 200 ካሬ ሜትር እንደሚሰጥ ማስታወቁን ገልጸዋል።

ለቦታው የካርታ ዝግጅት እየተካሄደ ባለበት ጉዳዩ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ መተላለፍ አለበት እንደተባለ አብራርተዋል።

በታህሳስ 2012 ዓ.ም የአስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ ይስጥበት የተባለው ጉዳይ አንድ ጊዜ አጀንዳው ካቢኔው ጋር አልደረሰም፣ ሌላ ጊዜ የመሬት ጉዳይ አሁን መታየት አቁሟል በሚሉ ምክንያቶች መፍትሔ አለማግኘቱን ነው አቶ ታደለ የገለፁት።

ማኅበሩ ጉዳዩ አልባት እንዲያገኝ የአዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮና የከተማውን ካቢኔ በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ተስፋ ሰጪ ምላሽ አለማግኘቱን አመልክተዋል።  

ቦታው ለማኅበሩ ካልተሰጠ የሚደግፋቸው ወገኖች ይበተናሉ ያሉት ባለሙያው ይህ እንዳይሆን አፋጣኝ መፍትሄ ጠይቀዋል።

ማኅበሩ ስለተፈቀደው መሬት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የነበሩ ግንኙነቶችን የሚያሳይ የሰነድ ማስረጃ መኖሩንም አክለዋል።

አርቲስት ተስፋዬ ገብረሃና በማኅበሩ የተያዙ ሕጻናትና ወጣቶች ተመልሰው ጎዳና ላይ እንዳይወድቁ ሁሉም የሚችለውን እገዛ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል።

የሙዳይ በጎ አድራጎት ማኅበር በ1992 ዓ.ም የተቋቋመ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ደርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም