ሀገር አቀፍ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት በነጻ ሊሰጥ ነው

88

አሶሳ ፤ ታህሳስ 8/2013 (ኢዜአ) በሀገር ደረጃ ከጥር 17 / 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለስድስት ቀናት የሚቆይ የማህጸን በር ካንሰር ክትባት በነጻ እንደሚሰጥ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በማህጸን በር ካንሰር ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጫ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ  በአሶሳ ከተማ ተካሄዷል።

በዚህ ወቅት በጤና ሚኒስቴር የማህጸን በር ካንሰር ክትባት አስተባባሪ አቶ መንግስቱ ቦጋለ እንዳሉት በሀገሪቱ በበሽታው የተጠቁ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ከልየታ ማዕከላት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የበሽታው ምክንያቶች ደግሞ ያለዕድሜ ጋብቻ እና ከበርካታ ሰዎች ጋር ጥንቃቄ የጎደለው ግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ ማነኞቹ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የበሽታው ስርጭት ለማቆም ስትራቴጂክ እቅድ ነድፎ እየሠራ መሆኑን አቶ መንግስቱ ተናግረዋል፡፡

ሥራው ቀጥሎም በሀገር ደረጃ ከጥር 17 እስከ 22/ 2013 ዓ.ም.  የማህጸን በር ካንሰር ክትባት በነጻ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችና ጤና ተቋማት ክትባቱ የሚሰጥባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ጠቅሰው   አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ በደርሶ መለስ አገልግሎቱን ለማድረስ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ክትባቱን ዕድሜቸው በ2013 ዓ.ም. 14 ዓመት የሆናቸው ሁለት ሚሊዮን 400 ሺህ ልጃገረዶች እንደሚያገኙ ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም በ2012 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዙር ክትባት ወስደው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሁለተኛውን ዙር ክትባት ያልደገሙትን እንደሚያጠቃልል ጠቁመዋል፡፡

ክትባቱ በመንግስት እና ግሎባል አሊያስ ፎር ኢሚዩናይዜሽን ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በትብብር እንደሚሰጥ አቶ መንግስቱ አመልክተዋል፡፡

በስትራቴጂክ እቅዱ ከ18 ዓመት በታች የሚደረግ ጋብቻን ማስቆም፣ መታቀብ፣ መወሰን እና ኮንዶም መጠቀምን በሚመለከት ግንዛቤ መፍጠር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ግንዛቤ ከመፍጠሩ በተጓዳኝ በሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎችና ሌሎችም የህክምና ማዕከላት ቅድመ ምርመራ በማድረግ በሽታው የከፋ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ ህክምና እንደሚሰጥ  አስረድተዋል፡፡

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጤና ቢሮ የክትባት አስተባባሪ አቶ ሻውል ተሰማ በበኩላቸው የማህጸን በር ካንሰር ህመምን አስቀድሞ ከመከላከል በተጨማሪ የከፋ ደረጃ ሳይደርስ ማከም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በሽታው ምንም ምልክት ሳያሳይ እስከ 20 ዓመት ሲቆይ ሞት ሊያስከትል እንደሚችል ጠቁመው ሴቶች ቅድመ ምርመራ በማድረግ ራሳቸውን እንዲጥብቁ  አሳስበዋል፡፡

በአሶሳ ትናንት በተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ 50 የሚጠጉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም