የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የዲጂታል ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደቱን የሚያግዝ ነው- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር

118

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) አገር በቀል የቴክኖሎጂ ኩባንያ መመስረት አገሪቱ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደት በማገዝ በኩል የሚኖረው አስተዋፆ ከፍተኛ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

መቀመጫውን በኢትዮጵያ ያደረገ ኢቴክ የተሰኘ አገር በቀል የቴክኖሎጅ ኩባንያ ተመስርቷል።

በምስረታው መርሃ ግብር ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛውን ጨምሮ ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

በእዚህም ሚኒስቴሩ የቴክኖሎጂ ኩባንያው በአገር ውስጥ መመስረቱ  የሚኖረውን ጠቀሜታ አመልክተዋል።

በተለይ አገሪቱ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደት በማገዝ በኩል ኩባንያው ያለው አስተዋፆ ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ሌሎችም እየተቋቋሙ ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው የኩባንያው መመስረት ኤጄንሲው የሚሰራውን የሳይበር ደህንነት የማስጠበቅ ሥራ የሚያግዝ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ባሉበት አገር ሆነው ያካበቱትን እውቀት፣ ልምድና ክህሎት ለአገራቸው ማካፈል እንዳለባቸው ተናግረዋል ።

በዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ በቀጥታ የዙም ውይይት ላይ ተገኝተው ሃሳባቸውን አካፍለዋል።

"የኩባንያው መመስረት ከኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀው በተለያዩ አገራት ሄደው ለቀሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በዘርፉ የድርሻቸውን አስተዋፆ እንዲያበረክቱ ያደርጋል" ብለዋል።

የኩባንያው መመስረት ኢትዮጵያ ወደ ቴክኖሎጂ አብዮት ለመግባት የጀመረችውን ሂደት እንደሚያግዝ የገለጹት ደግሞ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሽመልስ ገብረመድህን ናቸው።

ኢትዮጵያዊያን የዘርፉ ባለሙያዎች ከሀገር ውስጥና ከውጪ በመሰባሰብ ለአገራቸው ትልቅ አስተዋፆ እንዲያበረክቱ እድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

ኩባንያው መቀመጫውን ኢትዮጵያ ቢያደርግም ዓለማቀፋዊ ተደራሽነትን አንግቦ የተመሰረተ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጅ ድርጅት ስለመሆኑ በኩባንያው ኃላፊዎች ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም