ምግባረ ሰናይ ጠቅላላ ሆስፒታል ከአምስት ሚሊዬን ብር በላይ የሚያወጣ የህክምና ማሽን ድጋፍ ተደረገለት

196

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የሀንጋሪ ኢምባሲ ለምግባረ ሰናይ ጠቅላላ ሆስፒታል ከአምስት ሚሊዬን ብር በላይ የሚገመት 'ዲጂታል ኤክስ ሬይ' ማሸን ድጋፍ አደረገ።

ሆስፒታሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ስር የሚተዳደር ነው።

ድጋፉንም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹእ አቡነ ማትያስ እና ሌሎች አባቶች በተገኙበት ተረክቧል።

በኢትዮጵያ የሀንጋሪ አምባሳደር አቲላ ታማስ ኮፓኒ በዚህን ወቅት ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት እንዳላት ተናግረዋል።

ሁለቱ አገሮች ከ1960ዎቹ ጀምሮ በጤናው ዘርፍ  በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

ሀንጋሪ የሕክምና ቁሰቁሶችን በማምረት የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በድጋፉ የተበረከተው የራጅ ማሽንም የዚሁ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።

ሀገራቸው በተለይ በቤተክርስቲያን ስር ሆነው በክርስትና እሴት መሰረት የሚሰሩ ድርጅቶችን እንደምትደግፍና እንደምታበረታታም ነው ያነሱት።

ድጋፍ ሀንጋሪ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያበረከተችው አንድ ሚሊዬን ዩሮ የአካል መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

በቤተክርስትያኗ ፓትሪያርክ ልዩ ረዳትና የውጪ ጉዳዮች ኃላፊ እንዲሁም የድሬ ደዋና ጂቡቲ አገር ስብከት ኃላፊ ብጹእ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስትያኗን ወክለው ምስጋና አቅርበዋል።

ሆስፒታሉ ከክሊኒክ ጀምሮ ጠቅላላ ሆስፒታል መድረሱን አስታውሰው የዘመናዊ የህክምና መሳሪያ እጥረት እንደነበረበትም ገልጸዋል።

ድጋፉ በተለይ የተሻለ አገልግሎት ለማግኘት አቅሙ ለሌላቸው ዜጎች የሚያበረክተው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ስንታዬሁ ተፈራ በበኩላቸው ድጋፉ ሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ እንደሚያግዘው ገልጸዋል።

በድጋፍ የተበረከተው ማሽን ዘመናዊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሆስፒታሉ በመስኩ የሚሰጠውን አገልግሎት እስከ ሶስት እጥፍ ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም