ለምርጫው የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማድረግ ጀምረናል ... የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች

69

አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2013(ኢዜአ) ለስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ሁሉም ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ጫኔ ከበደ ፓርቲው በምርጫ ወረዳዎች አባላትን የመምረጥና የመመልመል ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ፓርቲያቸው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከሚገኙት 547 የምርጫ ወረዳዎች በ500 የምርጫ ወረዳዎች ላይ ለመሳተፍ እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል።

አሁን ባለው ሁኔታም በ435ቱ አደረጃጀቱን ለመዘርጋት እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

ኢዜማ በምርጫው አማራጭ የፖሊሲ ሀሳብ ለማቅረብ እንዲረዳው 46 ረቂቅ ፖሊሲዎች ማዘጋጀቱንና ከነዚህም ውስጥ ሃያዎቹ ጸድቀው የፓርቲው ፖሊሲ እንዲሆኑ መደረጉንም ዶክተር ጫኔ ገልጸዋል።

ለፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች አገራዊ ምርጫው ሰላማዊ፣ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲሆን ማበርከት ስለሚገባቸው አስተዋጽኦ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛልም ነው ያሉት።  

ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲካሄድ  የጸጥታ ጉዳይን በተመለከተ መንግስት ያለበትን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባው ጠቅሰው፤ ኢዜማ በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫ አስፈጻሚነት የሚመለምላቸው ግለሰቦችን ገለልተኝነት በሚመለከት በጥንቃቄ እንዲሰራም ጠይቀዋል።

ኢዜማ የዘንድሮው አገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለመገንባት ወደ ሚያስችል ምዕራፍ ለመሸጋገር ቁልፍ መሆኑን ያምናል ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ ሁሉም ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ  እንዲሆን በሃላፊነት ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ትዴፓ) ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን ፓርቲያቸው በትግራይ ክልል በነጻነት እንዳይቀሳቀስ አባላቱን ከማሰቃየት ባለፈ ፓርቲው በክልሉ የከፈተውን ጽህፈት ቤት ማፍረሱን አስታውሰዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል ከወሰደው የሕግ ማስከበር እርምጃ በኋላ ግን ሁኔታዎች መቀያራቸውንና ፓርቲው በክልሉ መንቀሳቀስ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል።

በመሆኑም አሁን ላይ ፓርቲያቸው የምርጫ ዝግጅት መጀመሩን ገልጸው፤ ምርጫው በሰላም እንዲካሄድም የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሰራም ጠይቀዋል።

መንግስት በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ስራ ማከናወኑ ትዴፓ ያለውን ዓላማ ለህዝብ ለማቅረብ እድል መፍጠሩን ገልጸው፤ ፓርቲያቸው ለምርጫው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ሳምንት ባወጣው የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫው በግንቦትና ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ይካሄዳል።

በጊዜ ሰሌዳው መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከየካቲት 8 እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የምረጡኝ ቅስቀሳ ያካሂዳሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ ይፋ ባደረገበት ወቅት በትግራይ ክልል ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት በቀጣይ የሁኔታዎችን አመቺነት ታይቶ በክልሉ ምርጫ የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያወጣ መግለጹ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም