የድምፅ ብክለት ባስከተሉ አንድ ሺህ ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዷል

1627

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት የድምፅ ብክለት ባስከተሉ አንድ ሺህ ተቋማት ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ የአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ኮሚሽን ገለፀ። 

ኮሚሽኑ የስድስት ወር አፈፃፀሙን ከክፍለከተማ እስከ ወረዳ ከሚገኙ የዘርፉ አካላት ጋር ገምግሟል፡፡

ኮሚሽነር ሲሳይ ጌታቸው እንደገለጹት በ5 ሺህ ተቋማት ላይ በተደረገ ቁጥጥርና ክትትል የድምፅ ብክለት በማስከተላቸው ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸው ያልታረሙ 1 ሺህ ተቋማት ከገንዘብ ቅጣት እስከ መታሸግ እርምጃ ተወስዶባቸዋል።

ሕጋዊ እርምጃው ከተወሰደባቸው መካከል ሆቴሎች፣ ጭፈራ ቤቶችና ኢንዱስትሪዎች ይገኙበታል።

በሌላ በኩል መዲናዋን ለማስዋብና አረንጓዴ ለማድረግ ከ142 ሺህ በላይ ወጣቶችን በማሰማራት ችግኞችን የመንከባከብና ደኖችን የመጠበቅ ስራ መከናወኑንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ለወጣቶች ድጋፍ በማድረግ ባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኖችን እንዲንከባከቡ በመደረጉ 80 በመቶዎቹ መፅደቃቸውን ነው የገለጹት።

የአረንጓዴ ልማት ስራን በሚፈለገው ደረጃ ለመከወን የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ወደ ስራ በማስገባት ከተማዋ  የለሙ ፓርኮችና ደኖች እንዲኖሯት ከከተማ እስከ ወረዳ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

አካባቢን ባለመንከባከብ ሊከሰት የሚችለውን የአየርና የውሃ ብክለት የሚያስከትሉትን የጤና እክል ያብራሩት አቶ ሲሳይ ሁለም አካባቢውን በአረንጓዴ በመሸፈን ሃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

በመጪው ክረምት 4 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በተለያዩ ቦታዎች ከወዲሁ የችግኝ ማፍላት ስራ መጀመሩንም ነው የገለፁት፡፡