በፓርቲ አባላት ላይ የሚደረገው ቁጥጥርና ክትትል ይጠናከራል ... ብልፅግና ፓርቲ

154

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2013 ( ኢዜአ) ሕገ-ደንብና አሰራርን ተከትሎ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎች ሥራቸውን መፈፀማቸውን ለመከታተል የሚያደርገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ብልጽግና ፓርቲ ገለጸ። 

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን የ2013 ዓ.ም የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው።

የፓርቲው ማዕከላዊ ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽነር አወቀ ኃይለማርያም እንዳሉት ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ከነበረው ኮሚሽን በአደረጃጀቱ የተለየ ነው።

ከዚህ ቀደም የነበረው ኮሚሽን የይስሙላና ጉባዔ ሲደርስ ሪፖርት የሚያቀርብ፤ በነበረው አሰራርም "እሴት የማይጨምር" መሆኑን ተናግረዋል።

ከለውጡ በኋለ ብልጽግና በአዲስ መልክ ሲዋቀር ኮሚሽኑ በአደረጃጀቱ ብቻ ሳይሆን ተልዕኮውን በተሻለ መንገድ ለማስፈጸም በሚያስችለው መልኩ መዋቀሩን ገልፀዋል።

አዲሱ አደረጃጀት የፓርቲውን የውስጥ ድርጅት ዴሞክራሲ እንደሚያጠናክርም ጠቁመዋል።

በተጓዳኝ ተልዕኮውን ሊያስፈጽም የሚችል ቋሚ የሰው ሃይል ከማዕከል እስከ ወረዳ እንዲሁም አስፈላጊው በጀትም በአባላት መዋጮ መመደቡን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በነበረው ኮሚሽን በአራት ክልሎች ብቻ ታጥሮ የነበረ መሆኑን አንስተው በአሁኑ አደረጃጀት ሁሉም ክልሎች ተሳታፊ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ኮሚሽኑን እስከታችኛው የፓርቲው እርከን አደረጃጀቱን መልሶ በማዋቀር ስኬታማ ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል።

በአንዳንድ ክልሎች የኮሚሽኑን አደረጃጀት ወጥነት ባለው መልኩ ገቢራዊ የማድረግ ችግር የታየ ቢሆንም በቀጣይ ይታረማል ብለዋል።

በሌላ በኩል ከፓርቲው ሕገ-ደንብ የሚቀዱ የአሰራር መመሪያዎችን በማዘጋጀት ኮሚሽኑ በስድስቱ ወራት ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የተግባርና የሃላፊነት መመሪያ መዘጋጀቱን አቶ አወቀ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በተቀመጠው አሰራር መሰረት በትክክል ወደ ሥራ መገባቱን የመከታተል ሥራ መሰራቱን አክለዋል። 

በቀጣይም በሁሉም ክልሎች የኮሚሽኑን አሰራር በተመለከተ የሃሳብና የተግባር አንድነት መፍጠር የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በአደረጃጀቱ የተጓደለ የሰው ሃይል በማሟላትና ሌሎች መሰረታዊ ችግሮችን በመፍታት የቁጥጥር ሥራውን የማጠናከር ሥራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።  

በተለይም በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚ አካላት ሥራቸውን ከፓርቲው ሕገ-ደንብና አሰራር ጋር የተጣጣመ መሆኑ ይፈተሻል ነው ያሉት።

ይህም ምደባ፣ ሹመት፣ ከሃላፊነት ማንሳት፣ የፓርቲው ሃብትና ንብረት አስተዳደርና ሌሎች የሥነ-ምግባር ጉዳዮች ላይ ቁጥጥሩ እንደሚጠናከር ገልጸዋል።

በዚህም ፓርቲው ጠንካራ ይሆናል፤ መንግሥት ያስቀመጣቸው ሁለንተናዊ የልማት፣ የዴሞክራሲና ሌሎች ሥራዎችንም በተሻለ መልኩ መፈጸም ያስችላል ብለዋል አቶ አወቀ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም